መጎልበት ያለበት በጎ እሴታችን – የቤተሰብ ጉባኤ!

በቤተሰብ አባላት መካከል የሚንጸባረቁ የመተሳሰብ እሳቤዎች ለማህበረሰብ እና ለሀገር እንደ መልካም ምሳሌ ሆነው የሚጠቀሱ ወሳኝ እሴቶች ናቸው፡፡

እነኚህ እሴቶች ከመልካም ቤተሰብ የሚወረሱ መልካም ሥብዕናዎች፣ የሥነምግባር እውቀቶች እና ልምዶች ናቸው፡፡

መተሳሰብ ያለበት ቤት ሰላሙ የተጠበቀ፣ ልጆች በነጻነት እና በስነምግባር የሚያድጉበት፣ ጥቂት የቤተሰብ አባላት ብቻ የተለየ ዋጋ የማይከፍሉበት፣ ሁሉም የቤተሰብ አባላት ችግሮችን በመነጋገር እና በመተሳሰብ የሚፈቱበት፣ ግጭቶች እና አለመግባባቶች በራሱ በቤተሰቡ የእርቅ ሥርዓት ወይም የቤተሰብ ጉባኤ አማካኝነት መቋጫ የሚያገኙበት፣ ጥቃቶች እና ጉልበት ብዝበዛዎች የማይሰሙበት ምቹና ሰላማዊ ስፍራ ነው፡፡ የዚህ ዋነኛ ምሰሶውም የመተሳሰብ እሴት የሚወልደው የሥነምግባር መርህ ነው፡፡ በተለይ የቤተሰብ ጉባኤ በቤተሰብ ውስጥ የሚገጥሙትን ስብራቶች ለመጠገን ሁነኛ መንገድ ሆኖ ለዘመናት ጥቅም ላይ የዋለ በጎ እሴታችን ነው።

ይሁንና የቤተሰብ ጉዳይ ረዘም ላለ ጊዜ ትኩረት ሳያገኝ በመቆየቱ የተነሳ በርካታ ችግሮች ሲከሰቱ፤ በቤተሰብ አባላትም ሆነ በሀገር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲደርስ ተስተውሏል፡፡

እንደሚታወቀው፤ ቤተሰብ ለማህብረሰብ ለውጥ ብሎም ለሀገር እድገት ጉልህ ሚና ስላለው ለቤተሰብ መሠረታዊ ጥበቃና ከለላ ሊደረግለት እንደሚገባ በማመን የአስፈጻሚ ተቋማትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ 1263/2014 መሠረት የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቤተሰብ ጉዳይን የሚመለከት ራሱን የቻለ ክፍል በማደራጀት የተለያዩ ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል።

ከእነዚህም መካከል ለቤተሰብ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ፣ ትግበራውን ለማሻሻል እንዲሁም የህብረተሰቡን ግንዛቤና ምላሽ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ በማሰብ በየአመቱ የሚከበረው የቤተሰብ ቀን በዋነኝነት ይገኝበታል።

የዘንድሮው የቤተሰብ ቀን “መተሳሰብ እንደቤተሰብ፤ ለሃገር እና ለማህበረሰብ” በሚል መሪ ቃል ግንቦት 7/ 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ2ኛ ጊዜ መከበሩ ይታወሳል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሁሉንም ቤተሰቦች በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ እንላለን፡፡

እኛም የቤተሰብ ቀንን ምክንያት በማድረግ ሊጎለብቱ ከሚገቡ በጎ እሴታችን መካከል አንዱ ስለሆነው የቤተሰብ ጉባኤ ያዘጋጀውን አጭር ማብራሪያ ቀጥሎ እናቀርባለን፡፡

የቤተሰብ ጉባኤ (Family Council) የቤተሰብ አባላት በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ በሚያደርጉት የጋራ ግንኙነት የሚካሔድ የቤተሰብ አባላት የውይይት መርሃ ግብር ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ የቤተሰቡ ጉዳዮች በሙሉ ተነስተው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ የቤተሰብ ጉባኤ ሰፋ ባለ ትርጉሙ በዝምድና የሚገናኙ ሌሎች ቤተሰቦችንም በመጨመር ሊካሄድ ይችላል፡፡

በጉባኤው የቤተሰቡ አባላት ሃሳብ በመስጠት ተሳፎ የሚያደርጉ ሲሆን የቤተሰብ ጉዳይ በአንድ ድምጽ እንዲረጋ የሚያስችል ስምምነት ይደረስበታል፡፡
በቤተሰብ ጉባኤ የቤተሰብ አባላት ስኬት እና ያሉበት ደረጃ፣ በአባላቱ ላይ የሚደርስ ችግር እና መፍትሔው፣ በቤት ውስጥ ስለሚኖር የቀጣይ ጊዜ የጋራ ጉዳይ እና የሥራ ክፍፍል ላይ ሁሉም አባላት ተሳትፈው ውይይት ይደረጋል፡፡

በውይይቱ ውጤትም የቤተሰብ የጋራ ጉዳዮች፣ ፈታኝ ሁኔታዎች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ለቤተሰብ ግንኙነት እና ትስስር የቤተሰብ ጉባኤ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በሂደትም ጤናማ ቤተሰብ ለመፍጠር በእጅጉ ያግዛል፡፡ ይህም ለማህበረሰብ ብሎም ለሃገር ይተርፋል፡፡

በቤተሰብ መካከል የጋራ ውሳኔዎች ህያው እና የማይቀሩ ናቸው፡፡ እነኚህ ውሳኔዎች በቤተሰብ አባላት እኩል ተሳትፎ እና ሃሳብ የሚጸኑት የቤተሰብ ጉባኤ ሲካሔድ ነው፡፡ እንዲሁም የቤተሰቡ አባል የሆኑ ልጆች ሃሳብ መስጠትን፣ ኃላፊነት መሸከምን፣ የችግር መፍቻ ክህሎቶችን እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችን ይለምዳሉ፡፡

ስለሆነም ሁሉም ቤተሰብ በሀገራችን ካሉን መልካም እሴቶች መካከል አንዱ የሆነው የቤተሰብ ጉባኤ እንዲጎለብት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መልዕክቱን ያስተላልፋል።

Please follow and like us: