የማህበራዊ ወግ ለውጥ ምንነት በጨረፍታ

ማህበራዊ ወግ በአንድ የተወሰነ አካባቢ በማህበረሰቡ አባላት ይሁንታ ተሰጥቷቸው የሚተገበሩ ድርጊቶችና አመለካከቶች ሲሆኑ ድርጊቶች ከትውልድ ትውልድ የመተላለፍ ባህሪ ያላቸውና ማህበረሰቡን እርስ በእርስ የሚያግባቡ፣ እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል እንዲፈጽም የሚያስገድዱ የወል ባህሪያት (collective behavior) ዉጤቶች ናቸው፡፡

የማህበረሰቡ የእርስ በእርስ ትስስር (interdependence) መሰረቱ ማህበራዊ ወግ ሲሆን መገለጫዎቹም የማህበረሰቡ አካል የሆኑ ግለሰቦች አንድን ተግባር በሚያከናዉኑበት ጊዜ ማህበረሰቡ የሚጠብቀውን (social expectation) ውጤት ከግምት ውስጥ በማስገባት በህገ ደንብ በመመራት ስምምነት የተደረሰበ ዉሳኔ የሚሰጡበት የእርስ በእርስ ትስስር ነው፡፡

የማህበራዊ ወግ ጽንሰ ሀሳብ አላማው የባህሪ ለውጥ ለማምጣት በአከባቢና በማህበራዊ የሰዎች ግንኙነት መካከል ያለውን ተጽእኖ ለመረዳት የሚስችል፣ የተፈቀዱና የተከለከሉ ተግባራትን የሚለይ፣ ህገ ደንብ ወይም መርህ ሲሆን በማህበረሰቡ የጋራ መግባባት ላይ በመመስረት ስምምነት የተደረሰበትንና አባላቱ መሆንና ማድረግ ያለባቸውን ወይም የሌለባቸውን የሚመራና የግለሰቦች ባህሪይ  የሚቀረጽበት ሂደት ነው፡፡

ማህበራዊ ወግ (Social Norm) የሚባሉት በአንድ የተወሰነ አካባቢ በማህበረሰቡ አባላት ይሁንታ ተሰጥቷቸው የሚተገበሩ ድርጊቶችና አመለካከቶች ናቸው።

እነዚህ ድርጊቶች ከትውልድ ትውልድ የመተላለፍ ባህሪ ያላቸውና ማህበረሰቡን እርስ በርስ የሚያግባቡ፣ እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል እንዲፈጽም የሚያስገድዱ የወል ባህሪያት ውጤቶች ናቸው።

ማህበራዊ የቁጥጥር ዘዴ በማህበረሰቡ የሚጠበቁ ባህሪያትን ለተከተሉ ማበረታቻ ላልተከተሉ ደግሞ ቅጣትን በመጣል እንድንጠብቃቸው ከማድረግ ባሻገር ብዙዎቻችን ይህንን በመፍራትና ማበረታቻን በመሻት ወጎቹን እንዴት እንደምናከብር የሚያመላክት ነው።

ሰዎች በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ እንዴት መኖር እንዳለባቸው እና እርስ በርሳቸው ለመከባበር የተለያዩ ማህበራዊ ውሎችን ያዘጋጃሉ፤ ግለሰቦችም ለዚህ ተገዥ ይሆናሉ።

ከእነዚህ መካከል ህግ፣ ግብረ-ገብነትና የማህበራዊ ወግ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ እነዚህ ሦስቱ የሰውን ድርጊት የሚገዙ መሰረታዊ ነገሮችና የማህበረሰብን አስተሳሰብና ድርጊት የሚወስኑ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።በእነዚህ ሦስት ጉዳዮች የማይተዳደር ግለሰብ መደበኛና ኢመደበኛ ቅጣቶችና ጫናዎች ይደርስበታል።

በህግ፤ ግብረ-ገብነትና ማህበራዊ ወግ መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ባህሪያቸውን መገንዘብና ሰዎች ለምን እንደሚያከብሯቸው በጥቂቱ ለመረዳት ህግ በአንድ ሀገር ውስጥ የዜጎችን መብቶች ጥቅሞች ለማስጠበቅና የአገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ የሚረዳ ስርዓት ነው።

ህግ ከፍተኛ ሥልጣን ባለው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ወይም ሕጋዊ እውቅና የተሰጠው ሲሆን እገዳ፣ ድንጋጌ፣ ትዕዛዝ፣ ደንብ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ ወይም አጠቃቀም መመሪያ ሊሆን ይችላል። ህግ ተፈጻሚነቱን የሚያረጋግጥ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን እንዲሁም ህጉን ለማይከተሉ ወይም ለማያከብሩ አካላት ተመጣጣኝ ቅጣትን የሚያስከትል ስርዓት ነው።

ግብረ ገብነት ደግሞ ሞራላዊ ግዴታ ያለው ከግለሰቡ ውስጣዊ ማንነት የሚመነጭና ከግለሰቡ ነጻነትና ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው። አንዳንድ ሰዎች ለሞራላቸው ወይም ግብረ ገብነታቸው የሚገዙት ውስጣዊ እርካታን ስለሚሰጣቸው ነው።

ሌሎች ደግሞ ግብረ-ገባዊ ተግባራትን መወጣት እርካታ ባይሰጣቸው እንኳን ግዴታ እንዳለባቸው ህሊናቸው ስለሚነግራቸው ይተገብሩታል። አንድ ግለሰብ እነዚህን ማህበራዊ ግዴታዎቹን ባለው መስተጋብር ወይም ጥቅማቸውን በማሰብ ሊተገብረው ይችላል።ነገር ግን ግለሰቡ ግዴታዎቹን ባይወጣ ከማህበረሰብ መገለልን የሚደርስበት ቅጣት ወይምውግዘት በመፍራትም ሊተገብራቸው ይችላል።

አንድን ድርጊት ሲያበረታቱ ወይም በተመሳሳይ ድርጊቱን ሲኮንኑ ያለው ስምምነት ነገሮችን ለመተግበር ቀላል ያደርገዋል። በተቃራኒው አንድ ድርጊት በአንዱ ማዕቀፍ ተቀባይነትን አግኝቶ በሌላው ማዕቀፍ ሲከለከል የሚፈጠር ተቃርኖ ወይም ግጭት ይኖራል። ይህንን መስተጋብር መረዳት የማህበራዊ ወግ ለውጥ ለማምጣት ቁልፍ ጉዳይ ነው።

በህግና በማህበራዊ ወግ መካከል የሚኖረውን ተቃርኖ ለመቀነስ ከተቻለም ለማስቀረት ህጉ ከመውጣቱ በፊትና ከወጣም በኋላ መታሰብ ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ህጉ ከመውጣቱ በፊት የህጉ መውጣት ድርጊቶቹን የበለጠ በድብቅ እንዲከናወኑ ያደርጋል ወይም ይህንንስ ለማስቀረት ምን መደረግ አለበት የሚለውን ማሰብ ተገቢ ነው።

ህጉ ከወጣ በኋላ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ስለ ህጉና ዓላማው የንቃተ-ህሊና ሥራዎችን ማከናወንና ማህበረሰቡ በፈቃደኝነት የህግ ተገዢ እንዲሆን ማሳመን ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው አንዱ አካሄድ ህግን ማክበር ራሱ አንድ ማህበራዊ ወግ እንደሆነ ለማህበረሰቡ ማስታወስ ነው። ለአብነትም በሀገራችን ‹‹በህግ አምላክ!›› የሚለው አባባል ለዚህ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

በሴቶች ህጻናትና አካል ጉዳተኞች  ላይ ጉዳት የሚያስከትሉና ሰብአዊ መብትን የሚገፉ አሉታዊ ወይም ጎጂ ማህበራዊ ወጎችን ለመቀየር የግለሰብን አመለካከትና ፀባይ መቀየር ያስፈልጋል። ሆኖም ግን የግለሰብ ባህሪ በራሱ በግለሰቡ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ግለሰቡ የሚኖርበት ማህበረሰብ ወግና ከግለሰቡ የሚጠበቁ ተግባራት እና ሌሎች አካባቢያዊ ሁኔታዎች ተጽእኖ ውጤት ነው።

የማህበራዊ ሳይንስ ጽሁፎችና ባለሙያዎች የግለሰብ ባህሪ በራሱ ተፈጥሮ ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነና ይልቁንም ከቤተሰብ ጀምሮ የማህበራዊ መስተጋብርና ትስስር ውጤት እንደሆነ ያስረዳሉ።

በአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ የግለሰብን አስተሳሰብ፣ አመለካከትና ባህሪ ለመቀየር በግለሰብ ላይ ከሚሰራው ሥራ ጎን ለጎን በቤተሰብ፣ በጓደኞች፣ በትምህርትና በሃይማኖት ተቋማት፣ በሚዲያ እና በሌሎችም በግለሰቡ ዙሪያ ባሉ ማህበራዊ ትስስሮች ላይ ጐን ለጐን መስራት ያስፈልጋል።

አሉታዊ ማህበራዊ ወግን ለመቀየር በክስተቱ ላይ ያለውን አመለካከት መለወጥ፣ ድርጊቱን ለመለወጥ የጋራ ውሳኔ ላይ መድረስ፣ በጋራና በትብብር ወደ ተግባር መግባት፣ ነባሩን ድርጊት ማስወገድና በአዲስ ለመተካት የማህበረሰቡን ነባር አስተሳሰብና እምነት በአዲስ መቀየር ያስፈልጋል።

ማንም ሰው አካል ጉዳተኛ ላለመሆን ምንም አይነት ዋስትና የለውም፡፡ የምንኖርባት ይህች ዓለም የአካል ጉዳተኞችና አካል ጉዳተኛ ላለመሆን ምንም ዋስትና የሌላቸው ሰዎች የሚስተናገዱባት ምድር መሆንዋን ለመረዳት በየእለቱ በማህበራዊ ኑሮዋችን የሚታዩ ገጠመኞች ማስተዋል ይገባል፡፡

ማንም ሰው አካል ጉዳተኛ ላለመሆን  ምንም ዓይነት ዋስትና የለውም የሚባለውም አካል ጉዳተኛነት በማንኛውም ሁኔታ፣ ጊዜና ስፍራ እንዲሁም በማንኛውም ሰው ላይ ከጽንሰት እስከ ህልፈት ሊደርስ ወይም ሊከሰት የሚችል አንዱ የህይወት አጋጣሚ ስለሆነ ነው፡፡ ስለሆነም የአካል ጉዳትና የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከግለሰብና ህብረተሰብ ባለፈ የአንድ አገርና የዓለም ህዝብ በአጠቃላይም የመላው የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ጉዳይ ነው፡፡

 

አካል ጉዳተኝነትን ከመረዳትና የአካል ጉዳተኞችን ችግሮች ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡና አስቸኳያ ማህበረሰባዊ ምላሽ ከሚሹት ዋናዋና ችግሮች መካከል የአመለካከት፣ የተግባቦት፣ የከባቢያዊ እና ተቋማዊ የሆኑ ችግሮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የአካል ጉዳተኞችን መበት ማጎልበትና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ በመንግስት ጥረት ብቻ በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም አስቸጋሪ ስለሚሆን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የአካል ጉዳተኛ ማህበራት ንቁ ተሳትፎና ተግባራዊ ምላሽ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡

መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ አሉታዊ አመለካከቶች በአዎንታዊ አስተሳሰብ መለወጥ የሚቻልበትን፣ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ለሚያገጥሙ የተግባቦት ችግሮች ፈጣን ምላሽ የሚያገኙበትን፣ አገልግሎት ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል በሚሰማሩበት ቦታ ሁሉ ምክንያታዊ ማመቻቸት ተግባራዊ የሚሆንበትን እና የአካል ጉዳተኞች አካታችነት በሁሉም ዘርፍ ተቋማዊ በማድረግ ተፈጻሚ የሚሆንበትን ምቹ መደላደል ከመፍጠር በተጓዳኝ አካል ጉዳተኛ ማህበራት ራሳቸውን እንዲችሉና አባላቶቻቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ ጠንካራ ቁመና ላይ እንዲገኙ ለማስቻል በቀጣይ የሚያደርገው ሁለንተናዊ ክትትልና ድጋፍ በበለጠ ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በዚህ መሰረት የሰው ልጆች ሁሉ የሰብዓዊ መብቶቻቸው በእኩልነትና ያለምንም ልዩነት መከበር እንዳለበት በመገንዘብ የአካል ጉዳተኞችን መብት እንደማንኛውም ዜጋ ማክበርና በህዝብ አገልግሎቶችና ዕድሎች እኩል ተደራሽና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከመንግስት መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከመላው ማህበረሰባችን ይጠበቃል፡፡

በዓለማየሁ ማሞ

ዋቢ መረጃ ፡- አሉታዊ የማህበራዊ ወግ ለውጥ ማንዋል  

     ሴ/ህ/ወ/ – 2012 ዓ.ም

Please follow and like us: