በአዲስ አበባ ከተማ በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት 6136 (የድሃ ድሃ የሆኑ ቤተሰቦች) ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ ተገለፀ ።

በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ድጋፍ የትግበራ ሂደት ግምገማ ላይ በተዘጋጀው መድረክ እንደተገለፀው በአዲስአበባ ከተማ ለሚገኙ በጥናት ለተለዩ 6136 የድሃ ድሃ የሆኑ ቤተሰቦች ድጋፍ መደረጉ ተገለፀ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለፁት በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ከአለም ባንክ የተገኘውን ውስን ሃብት በማቀናጀት የድሃ ድሃ የሆኑ ቤተሰቦች በ20 ከተሞች ተለይተው በአገልግሎት ሰጪዎች አማካይነት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል። ሚኒስትራ እንደገለፁት ከነዚህ ከተሞች መካከል በመዲናዋ ለሚገኙ ጉልበት የሌላቸው በቋሚ ቀጥታ ድጋፍ እንዲሁም ጉልበት ያላቸው በማህበረሰብ ስራዎች እየተሳተፉ ተጠቀሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አክለውም በዚህ ፕሮጀክት በተጨማሪነትም በተለይም ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ በርካታ ዜጎች ከጎዳና ላይ ተነስተው በማቋቋሚያ ማዕከላት ከመሰረታዊ የምግብ፣ መጠለያና አልባሳት አቅርቦት ባሻገር የስብዕና ግንባታ እና የህይወት ክህሎት ስልጠናዎችን በመውሰድ ከቤተሰብና ማህበረሰብ ጋር በመቀላቀልና በመዋሃድ ከነበሩበት አስከፊ ህይወት እንዲላቀቁና የመጨረሻው አላማ የሆነውን በዘላቂነት ማቋቋም የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንደሆነ ገልፀዋል ።

ይህ የድጋፍ ትግበራ ሂደት ግምገማ ከአጠቃላይ የተጠቃሚዎች ቁጥር 44 ፐርሰንቱ በከተማዋ የሚገኙ መሆናቸው የችግሩን ስፋት የሚያሳይ በመሆኑ ይህ መድረክም አገልግሎት ሰጪዎች ያጋጠሟቸውን ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ከቢሮው ጋር በመተባበር አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚረዳ ገልፀዋል።በመድረኩ ላይ የተገኙት የአገልግሎት ሰጪዎች በበኩላቸው በፕሮጀክቱ የትግበራ ሂደት ወቅት ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የቦታ፣የማቋቋሚያ ማዕከላት ኪራይ ዋጋ፣ የግንዛቤ እጥረት፣ ከቤተሰብና ማህበረሰብ ጋር በመቀላቀል ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችና ሌሎች ችግሮችን አንስተው ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከአዲስአበባ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በቅንጅት ምላሽና የመፍትሔ አቅጣጫ ተሰጥቶበታል።በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት በአጠቃላይ 13,360 መጠለያ አልባ ዜጎችን በ20 ከተሞች ውስጥ እየደገፈ ይገኛል።

Please follow and like us: