ቋሚ ኮሚቴው የአስፈጻሚ አካላት እቅድ ለስርዓተ ጾታ ጉዳይ ትኩረት የሰጠ መሆኑንና በተገቢው በጀት መደገፉን የመከታተልና የማረጋገጥ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል

ቋሚ ኮሚቴው የአስፈጻሚ አካላት እቅድ ለስርዓተ ጾታ ጉዳይ ትኩረት የሰጠ መሆኑንና በተገቢው በጀት መደገፉን የመከታተልና የማረጋገጥ ስራው አጠናክሮ እንደሚቀጥል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገለጹ።

ለስርዓተ ጾታ ጉዳይ ምላሽ ሰጪ የበጀት ስርዓት ማበጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የህግ አውጪ አካላትን ግንዛቤና ሚናቸውን ለማሳደግ ያለመ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል። በመድረኩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወርቅሰሙ ማሞ  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አካታችነትን፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀመራቸው ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል። ምክር ቤቱ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በጋራ በመሆን ህግ በማውጣት፣ በአስፈጻሚ አካል ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ በግብረ መልስ አሰጣጥ ሂደት የማይተካ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል። ጥረቱ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ወደፊትም በቅርበት ተደጋግፈን መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው የአስፈጻሚ አካላት እቅድ ለስርዓተ ጾታ ጉዳይ ትኩረት የሰጠ መሆኑንና በተገቢው በጀት መደገፉን የመከታተልና የማረጋገጥ ስራው አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው የዜጎችን በተለይም ደግሞ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት ሁለንተናዊ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። በሌሎች አካላት አብይ ተግባራት ውስጥ ፍላጎታቸው ተለይቶ ጉዳያቸው እንዲካተትና እንዲፈፀም ሰፊጥረት ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለአካቶ ትግበራ ስልትና ሂደት መሳለጥ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት፣ የተቋማትን አቅም በመገንባት፣ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ስራዎችን በማከናወን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡ የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ በሁሉም ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ አካታች በሆነ መልኩ በመተግበር ረገድም መልካም ጅምሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ሆኖም አሁንም ከበጀት፣ ከአደረጃጀት፣ ከቁርጠኝነት አንጻር ክፍተት መኖሩን እና ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድ የተገኘው ውጤት በሚፈለገው ደረጃ አለመድረሱን በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ተቋማት አካቶ ትግበራ ሂደቱ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን መሥራት እንዳለባቸው ተናግረው በዚህ ረገድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በተለይም ተቋማት እቅድ በሚያዘጋጁበት ወቅት ለሥርዓተ ጾታ እንዲሁም ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትኩረት የሰጠ እንዲሆን በክትትልና ቁጥጥር ሥራቸው እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርበዋል። በመድረኩ ሌሎች የሴቶችና ህጻናት መብት ከማስጠበቅ አኳያ የቋሚ ኮሚቴውን ድጋፍ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

Please follow and like us: