“ከሚያዝያ እስከ ሚያዝያ ” የፀረ አደንዛዥ እፆች እና አሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል አገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በመካሄድ ላይ ነው።

“ከሚያዝያ እስከ ሚያዚያ ” የፀረ -አደንዛዥ እጾችና አሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችን የመከላከል አገራዊ ንቅናቄና የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአድዋ የድል ሙዚየም እየተካሄደ ይገኛል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በንቅናቄ መድረኩ ላይ እንደገለጹት ፣ኢትዮጵያ በራሳቸው ባህልና ታሪክ የሚኮሩ ወጣቶች እንደሚያስፈልጓት ገልፀዉ ለዚህም ቤተሰብ፣ የሀይማኖት አባቶችና ተቋማት ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም መላው ማህበረሰብ በከፍተኛ ኃለፊነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል ። ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት አደንዛዥ እጾች ወጣቶችን ለጤና ችግሮች ፣ ለኢ-ሞራላዊ ድርጊቶችና ለአገር አፍራሽ ተልዕኮዎች እንዲጋለጡ እንደሚያደርግ ገልፀዋል ።

በስነ ምግባር የታነጹ፣ ጤናማና አምራች ወጣቶችን ለማፍራት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ መስራት እንደለበት አስገንዝበዋል ። አሉታዊ መጤ ልማዶችና አደንዛዥ እጾች የወጣቱ ብሎም የሁሉም ማህበረሰብ የጊዜው ፈተና እንደሆነም ሚኒስትሯ ተናግረዋል ።በተለይም የወጣትነትን መንፈስ በእጅጉ እየቀማ እንደሚገኝም ጠቁመዋል ። አክለውም የችግሩን አሳሳቢነት ለመቅረፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ሊያግዙ እንደሚገባም ገልጸዋል ።

የአንድ ዓመቱ የንቅናቄ አፈጻጸም ሪፖርትም በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ሙና አህመድ የቀረበ ሲሆን ውይይትም ተካሂዷል ። በሪፖርቱ እንደተመላከተውም የአደንዛዥ እጽ ስርጭትን በመከላከልና በመቆጣጠር ሂደት 12,962 በላይ ሺሻ መጠቀሚያ እቃዎች እና 70 ኪሎ ግራም አደንዛዥ እጽ መወገዱ ተጠቅሷል ። በተጨማሪም በዚህ አንድ አመት ውስጥ በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 3241 የስፖርታዊ ውርርድ(betting ) ቤቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል ።

በመድረኩ ለይ የህዝብ ተወከዮች ምክር ቤት ማህበራዊ ልማት፣ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ሚኒስትር ድኤታዎች ፣የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣የወጣት አደረጃጀት ኃላፊዎች እንዲሁም የፌዴራልና የክልል ተቋማት ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

 

Please follow and like us: