የኢፌዴሪ የሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ2 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ ያስገነባውን የህፃናት ማቆያ አስረከበ

የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአርባምንጭ ማረሚያ ተቋም ጊቢ ውስጥ ያስገነባውን የህፃናት  ማቆያ ለአርባምንጭ ማረምያ ተቋም፣ለአርባምንጭ ከተማና ለዞኑ ሴቶችና ህፃናት መምሪያ አስረክቧል።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት አለሚቱ ኡሞድ የህፃናትን መብት ለማስከበርና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ በማረሚያ ተቋማት የሚያድጉ ታዳጊ ህጻናት ከተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ተለይተው ስለሚያድጉ ህፃናቱ ሁሉ አቀፍ እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማስቻል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ማቆያውን ማስገንባቱን ተናግረዋል።

ማዕከሉ 2 ሚሊዮን 946 ሺ ብር በፈጀ ወጭ መገንባቱን ተመላክቷል። የህፃናት መዋያ ስፍራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በስነ-ምግባር የታነፀ በስነልቦና የዳበር ጤናማና አምራች ዜጋን መፍጠር ይገባልም ብለዋል። ማቆያው በውስጥ ቁሳቁስ እንዲሟላ የሚመለከተቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረምያ ቤቶች አስተዳደር  ኮሚሽን ኮሚሽነር አለማየው ማሞ በበኩላቸው  ህፃናት ላይ መስራት ሀገር ላይ መስራት እንደመሆኑ ለህፃናት ሁሉ አቀፍ እንክብካቤ ለማድረግ  የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው እና በቀጣይ ታራሚ ወላጆችም በቅርበት እንዲኖሩ ለማስቻል የተጀመረው የማረሚያ ቤት ግንባት ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶች እና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ካሰች ኤልያስ በበኩላቸው በቀጣይ በማዕከሉ ቀሳቁሶችን ከሟሟላት ባሻገር ከጤና እና ከትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የቅድመ መደበኛና የድህረ መደበኛ ትምህርት የሚያገኙበት ሂደት ለማመቻቸት በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ህፃናት ያለ ወላጆቻቸው ምቹ ባልሆነ ሁኔታ እንዳያድጉ በማሰብ ለማቆያው መገንባት የድርሻቸውን ለተወጡ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የበጎ አድራጎት ድርጅቱን አመስግነዋል ሲል የዘገበው የጋሞ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ነው።

 

Please follow and like us: