የህጻናት የቀን ማቆያ ተንከባካቢዎች የስልጠና ስርዓተ – ትምህርት ቀረጻ እየተካሄደ ነው

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኮተቤ የድረምረቃ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የህጻናት የቀን ማቆያ ተንከባካቢዎች ስልጠና ስርዓተ – ትምህርት ቀረጻ ላይ ባለድርሻ አካላት ምክክር አካሂዷል።

በመድረኩ የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ ህጻናት እንደተናገሩት፤ ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንደመሆናቸው ተገቢው ድጋፍና እንክብካቤ እያገኙ በስነምግባር ታንጸው በአካልና በአእምሮ ዳብረው ማደግ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለይ በተቋማት አካባቢ ምቹ የስራ ሁኔታ ለመፍጠር፣ የሴቶችን የስራ ጫና ለመቀነስና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ብሎም የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ደረጃቸውን የጠበቁ የህጻናት የቀን ማቆያዎችን ለማስፋፋትና ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ሆኖም በህጻናት የቀን ማቆያዎች የሚሰጠው የእንክብካቤ አገልግሎት ተገቢው ክህሎት ባላቸው ሞግዚቶች የታገዘ ሊሆን ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኮተቤ የድረምረቃ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የህጻናት የቀን ማቆያ ተንከባካቢዎች የስልጠና ስርዓተ – ትምህርት ቀረጻ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የስርዓተ – ትምህርቱ መቀረጽ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ያለው የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ብቃት ያላቸውን ሙያተኞችን ለማፍራት ብሎም ህጻናት ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ የእንክብካቤ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል። ስርዓተ – ትምህርቱ በስራ ላይ ከመዋሉ በፊት በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ግብዓት እንዲሰጡበትና በውይይት እንዲያዳብሩት ለማስቻል ታስቦ መድረኮች እየተዘጋጁ መሆኑን አስገንዝበዋል። ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ሁሉም ለተሻለ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና የተሳካ ትግበራ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።

 

Please follow and like us: