የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሀ ግብር 30ኛ አመት ሀገር አቀፍ ግምገማና ሪፖርት ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር ተካሄደ ።

በመርሀ ግብሩ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ  ኢትዮጵያ የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀረጹና በትግበራ ላይ የሚገኙ የተለያዩ አለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶችን በመፈረምና የህጓ አካል እንዲሆኑ በማድረግ እየተተገበረች እንደምትገኝ ገልጸዋል ።

ከነዚህም መካከል የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሀ ግብር በዋናነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ሲሆን የድርጊት መርሀ ግብሩ እ.ኤ.አ በ1995 ከወጣ ጀምሮ ይህንን ሰነድ በመቀበልና ሀገራዊ የድርጊት መርሀ ግብርም በማዘጋጀት ስትተገብር መቆየቷን ገልፀዋል ።

ሚኒስትሯ አክለውም በያዝነው በጀት ዓመት የቤጂንግ 30ኛ ዓመት በማስመልከት ኢትዮጵያዊ ሀገር አቀፍ ግምገማና የሪፖርት ዝግጅትን ያከናወነች መሆኑን ጠቅሰው የሪፖርቱን ጥራትና ተአማኒነት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የመንግስት ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሴት አደረጃጀቶች እና የሪፖርት ዝግጅቱ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት የግብዓት ማሰባሰቢያ መርሃግብር በማዘጋጀት ሪፖርቱ እንዲዳብር መደረጉን ገልፀዋል።

በመድረኩም ሀገራዊ ግምገማውንና ሪፖርቱን ይፋ ለማድረግ የሪፖርቱን ይዘት በመመልከት በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ የአስተባባሪና ቴክኒክ ኮሚቴዎች፣ባለድርሻ አካላት የተለያዪ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ሚኒስትር ድኤታዎች፣ ከሴክተራቸው አንፃር  ተሰርተው በረቂቁ ያልተካተቱ ስራዎች ላይ ግብዓት  ተሰጥቶበታል።

የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሀ ግብር በ12 የተለዩ የትኩረት ነጥቦች መሰረት ሀገራት በየአምስት አመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶችን እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲገመግሙ የሚጠይቅ ሲሆን ኢትዮጵያም የቤጂንግ+5 ግምገማ እ.ኤ.አ በ1999፣ ቤጂንግ+10 በ2004፣ ቤጂንግ+15 በ2009፣ ቤጂንግ+20 በ2014 እንዲሁም ቤጂንግ+25 ደግሞ በ2019 በማከናወን ለሚመለከታቸው አካላት አቅርባለች።

 

Please follow and like us: