የተጠቃለለ የህፃናት ህግ አስፈላጊነት፣ ችግሮቹና መፍትሔዎቹ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሄደ

ህጻናትን የተመለከቱ ህጎችን ከአለም አቀፍ ህጎች ጋር ማጣጣም እና ወጥ የሆነ የተጠቃለለ የህፃናት ህግ ማዘጋጀት አስፈላጊነት፣ ችግሮቹና መፍትሔዎቹ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሄደ።

መድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው። በመድረኩ ህጻናት ለጥቃት ተጋላጭ እንደመሆናቸው የተለየ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው። ለዚህም ጠንካራ የህግ ማዕቀፎች ሊኖሩ እንደሚገባ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህጻናት መብትና ደህንነት መሪ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ ገልጸዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያ የህጻናትን መብትና ደህንነት በማስከበር ረገድ አርአያ ብትሆንም በሀገራችን ህጻናትን የሚመለከቱ ህጎች በተለያዩ ሰነዶች ተበታትነው የሚገኙ በመሆኑ በአፈጻጸም ሂደቱ ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መብቶች ኮንቬንሽንና በአፍሪካ የህፃናት መብት ደህንነት ቻርተር ባቀረበቻቸው የአፈጻጸም ሪፖርቶች ላይም የተጠቃለለ የህጻናት ህግ ባለመካተቱ እንደክፍተት ሲነሳና በተደጋጋሚ ምክረ ሃሳብ ሲሰጥበት መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ ስለሆነም ከአለም አቀፍና ሀገራዊ ህጎች፣ ከሀገራችን ባህልና እሴቶች ጋር የተጣጣመ፣ ወቅቱን ያገናዘበ እንዲሁም የህጻናትን መብትና ደህንነትን በተሟላ መልኩ ለማስጠበቅ የሚያስችል፣ ለአሁኑና ለወደፊትም ጭምር የሚያገለግል የተጠቃለለ ህግ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም ችግሩን ለመቅረፍ ቀደም ሲል ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ጥናት መካሄዱንና ያሉትንም ክፍተቶች ለመለየት ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል። በቀድሞ ጥናት ያልተካተቱትን በመፈተሽ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣምና ወቅታዊ እንዲሆን ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

የተጠቃለለ ህጉ መኖሩ ለህብረተሰቡም ሆነ ለባለሙያው ሰነዱን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ፣ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ብሎም ቀልጣፋና ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት በእጅጉ ያግዛል ብለዋል። በተጨማሪም የተጠቃለለ የሕፃናት ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ለፍትህ እና ሰብአዊ ክብር ያለን የጋራ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑንም አስገንዝበዋል። በመሆኑም የህጻናቱን የወደፊት ህይወት ለማቀናት፣ ህልማቸውን እውን ለማድረግ እና በዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት በህጻናት ዙሪያ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በመድረኩ በተጠቃለለ ህጉ አስፈላጊነት፣ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮችና የመፍትሔ ሃሳቦች ዙሪያ እንዲሁም በሰነድ ዝግጅት ሂደቱ ዙሪያ መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። በመርሀ ግብሩ ላይ በህጻናት ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

Please follow and like us: