የሌማት ትሩፋት የስራ ባህልን በመቀየር የገቢ ምንጭ ሆኗል – ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ   

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የስራ ባህልን በመቀየር የገቢ ምንጭ ሆኗል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።

ሚኒስትሯን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በሐረሪ ክልል ከተማና ገጠር ወረዳዎች ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። በዚህ ወቅት ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጌጎ ተስፋዬ፤ በክልሉ በአነስተኛ መሬት ላይ የሚከናወኑ የአትክልትና የእንስሳት እርባታ ልማት ምርታማነት እንዲጎለብት ማስቻሉን ከጉብኝታቸው መረዳታቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ቀደም ሲል በጫት ምርት ይሸፈን የነበረው ማሳ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የጓሮ አትክልቶች እየለሙ መሆኑንና አርሶ አደሩ የስራ ባህሉን እንዲቀይር ማስቻሉን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም በዶሮ፣ በከብት እርባታና በንብ ማነብ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ከስራ ጠባቂነት ተላቀው ስራ እንዲያገኙና እንዲለወጡ ማድረጉም እንዲሁ።

የሌማት ትሩፋት ስራዎች የአርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን  እንዲያረጋግጥ ማስቻሉንም አመልክተዋል። የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ከቁሳቁስና ከኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን መመልከታቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ችግሩን መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ታንኳይ ጆክ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚከናወኑ የሌማት ትሩፋት ስራዎች መሬት ፆም እንዳያድር በማድረግ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ መመልከታቸውን ገልጸዋል። ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈም አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የዋጋ ንረትን እያረጋጋ መሆኑንም እንዲሁ።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር፤ በክልሉ ከተማና ገጠር ወረዳዎች ላይ በርካታ ማህበረሰብ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተሰማርተው እንደሚገኙ አብራርተዋል። ከተሰማሩባቸው ዘርፎች መካከልም አትክልትና ፍራፍሬ፣ ዶሮ እርባታ፣ ከብት ድለባና ንብ ማነብ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። በስራውም ወጣቶች፣ ከስደት ተመላሾች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች የገጠርና የከተማ የማህበረሰብ ክፍሎት በዘርፉ ተሰማርተው የስራ እድል እያገኙበትና ለነዋሪው ምርቶችን በማቅረብ የዋጋ ንረትን እያረጋጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉም የስራ ባህልን በመቀየር ማህበረሰቡን ከተረጂነትና ከጠባቂነት እያላቀቀ የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠ ነው ብለዋል። በጉብኝቱም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ በቀጣይም ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር ውይይትያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው ኢዜአ ነው

Please follow and like us: