በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች 2 ሺህ የጤና ማዕከላትን መገንባት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች 2 ሺህ የጤና ማዕከላትን ለመገንባት የጤና ሚኒስቴርና ሌሎች ሦስት ተቋማት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ።

ሥምምነቱን የጤና ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲና የሩስያ ፓን-አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት የተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ተወካዮች ፈርመውታል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በዚህ ጊዜ፤ በሥምምነቱ መሠረት ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመታት እንደሚቆይና 2 ሺህ የጤና ማዕከላትን ለመገንባት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ማዕከላቱ በዋናነት በእናቶችና ሕጻናት ጤና፣ በአረጋውያን፣ በወጣቶች እንዲሁም በወሊድ፣ በክትባት፣ በቤተሰበ እቅድና በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ተጠቁሟል።   ይህም ለማኅበረሰቡ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ነው ያሉት። የሚገነቡት የጤና ማዕከላት እያንዳንዳቸው ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ የሚጠጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የተለያዩ የሕክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል። ማዕከላቱን ለመገንባት ከ250 ሚሊየን ዶላር በላይ እንደሚፈጁና ወጪውም በሩስያ ፓን-አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት የሚሸፈን መሆኑ ጠቁመዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው፤ ሥምምነቱ የእናቶችን ብሎም የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል። በመሆኑም ሚኒስቴሩ ለፕሮጀክቱ እውን መሆን የሚጠበቅበትን ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

የሩስያ የፓን-አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት ግብረ-ሰናይ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኦክሳና ማዮሮቫ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ የዜጎችን ጤናማ ሕይወት ለማስጠበቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ  ይህን ፕሮጀክት ወደ ሀገሪቱ እንዲመጣ ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ እውን መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ(ዶ/ር) ናቸው። ዛሬ ከተለያዩ አካላት ጋር የተደረገው የሥምምነት ፊርማ እውን እንዲሆን እንደሚሰራ ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

 

Please follow and like us: