ወጣቶችን ድምፃቸውን ለማሰማትና ሀሳባቸውን ለመለዋወጥ የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ሆነ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ጋር በመተባበር ዩ ሪፖርት ኢትዮጵያ /’U-Report Ethiopia’/ የተሰኘ የአፕ መተግበሪያ ይፋ አደረገ።

መተግበሪያውን ይፋ ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ መተግበሪያው የሀገራችን ወጣቶች በተለይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲለዋወጡ እና ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል። በተጨማሪም ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ከወጣቶቹ ለማሰባሰብ የሚያስችል ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል። የወጣቶችን ድምጽና ሃሳብ የምንሰማበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ ወጣቶች መተግበሪያውን በመጠቀም ለዘላቂ ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በጥልቀት እየመከረች የምትገኝ ወቅት በመሆኑ ወጣቱ በንቃተ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ወጣቶች መተግበሪያውን ፍሬያማ በሆነ መንገድ፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲገለገሉም በአፅዕኖት አሳስበዋል። ለመተግበሪያው እውን መሆን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ዩኒሴፍ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር አቡበከር ካምፖ በበኩላቸው ‘U-Report Ethiopia’ ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል የአፕ መተግበሪያ ሲሆን በ99 የዓለም ሀገራት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረ መሆኑንና ኢትዮጵያን 100ኛ ሀገር ሆና መቀላቀሏን ገልጸዋል። አብዛኛው ወጣት የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግና ለማብቃት ታስቦ መዘጋጀቱንና ወጣቶችም በንቃት እየተሳተፉበት ያለ ውጤታማ መተግበሪያ ለመሆኑ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማሳያነት አቅርበዋል።

በማስጀመሪያ መርሐግብሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የዩኒሴፍ ዳይሬክተር አቡከር ካምፖ (ዶ/ር)፣ የወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሙና አህመድ እና ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

Please follow and like us: