በሱማሌ ክልል በጎዴ ዞን ኢላን ቀበሌ የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት የተቀረጹ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም የመስክ ጉብኝት ተካሄደ

በሱማሌ ክልል በጎዴ ዞን ኢላን ቀበሌ የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት የተቀረጹ ፕሮጀክቶች ትግበራና አፈጻጸም አስመልክቶ የመስክ ጉብኝት ተካሄዷል።

በጉብኝቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምክትል ዳይሬክተር፣ የክልሉ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ፣ የፓስቶራሊስት ኮንሰርን ኃላፊዎችና የቦርድ አባላት፣ የስፓኒሽ የልማት ድርጅት ምክትል ኃላፊ፣ የሁሉም ወረዳ የጽ/ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም የጎዴ ከተማ አስተዳደር ተሳትፈዋል። በጎዴ ዞን ኢላላ ቀበሌ በህብረት ስራ የተደራጁ 200 ሴቶች ፓስቶራሊስት ኮንሰርን በተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት በተደረገ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ በእርሻና በከብት ዕርባታ ዘርፍ እንዲሰማሩ በመደረጉ ኑሯቸው መሻሻሉን መመልከት ተችሏል።

ፕሮጀክቱ ሴቶችን በኢኮኖሚ ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ የኢኮኖሚ ብቃት እንዲኖራቸውና በማህበረሰቡ ዘንድም ያላቸውን ተቀባይነት ከፍ እንዲል የበኩሉን እገዛ ማድረጉን በተካሄደው የመስክ ጉብኝትና ከተጠቃሚዎች ጋር በተደረገው ውይይት ማረጋገጥ ተችሏል። በፕሮጀክቱ የታቀፉ ሴቶች እየተደረገላቸው ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፤  በስራ ሂደት ያጋጠሟቸውን ችግሮች አንስተው ተወያይተዋል። በአካባቢያቸው በተለይ የዕጽዋት በሽታዎች መኖር እንዲሁም ጎርፍ እያስከተለ ያለው ጉዳት እና የነዳጅ መወደድ ለተጨማሪ ወጪ እየዳረጋቸው መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ለእጽዋት በሽታውና ጎርፉ በምርት ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው፣ በሶላር የሚሰራ ፓምፕ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸውና የፕሮጀክቱ ስራም እንዲስፋፋ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። በመስክ ምልከታውና ከሁሉም ወረዳ ከመጡ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር በተደረገው ውይይት ፕሮጀክቱ ሴቶች ከቤት ውስጥ ስራ ባሻገር ተጨማሪ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ ማስቻሉ ተገልጿል። ፕሮጀክቱ እንዲስፋፋና ሞዴል ቀበሌ እንዲሆን ለማስቻልም ከፌደራል ሴክተር መ/ቤቶች፣ ከክልልና ከዞኑ ድጋፍ እንደሚሹ ለዚህም ሁሉም በትብብር እንዲሰራ መግባባት ተፈጥሯል።

ሴቶችም ችግራቸውን በራሳቸው አቅም መፍታት እንዲችሉ ይበልጥ መደራጀት እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከመስክ ምልከታው ጎን ለጎን በዕለቱ ለተደራጁት ሴቶች ለእርሻ አገልግሎት የሚውል የትራክተር ድጋፍ ተደርጓል። የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በፕሮጀክቱ ቀጣይነት እንዲሁም ከሚኒስቴር መ/ቤቱ እና ከክልሉ ጋር በጋራ መስራት በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከስፓኒሽ የልማት ድርጅት፣ ከፓስቶራሊስ ኮንሰርን ኃላፊዎችና ከቦርድ አባላት ጋር በመወያየት ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት እንዲወስድ የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጠል።

Please follow and like us: