አዲሱ ሀገራዊ የልማት ፕሮግራም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን አካታችና ተደራሽ ያደረገ እና ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሊሆን ይገባል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

የተባበሩት መንግስታት የስህዝብ ልማት ፈንድ (UNFPA ) ኢትዮጵያ ባዘጋጀው 10ኛው ሀገራዊ የልማት ፕሮግራም ላይ ባለድርሻና አጋር አካላት ምክክር አካሂደዋል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ዩኤን ኤፍ ፒ ኤ(UNFPA ) ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር ለስርዓተ ጾታ እኩልነት እና ሴቶችን ለማብቃት ቅድሚያ የሰጡ ብሎም ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን፣ የህጻናት ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን መከላከልና በአፍላ ወጣቶች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ሰፊ ርብርብ ማድረጉን ገልጸዋል። በተለይ ያለዕደሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ ብሎም ጥቃት ለደረሰባቸው ወገኖች በአንድ መስኮት ማዕከል እና በማረፊያ የሚሰጠው አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል ዩኤን ኤፍ ፒ ኤ(UNFPA ) የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከቱን እና ለስኬታማነቱ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ሆኖም በሀገሪቱ በደረሱ የተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተጋላጭ ዜጎች መኖራቸውን ክብርት ሚኒስትሯ ጠቁመው አዲሱ የልማት ፕሮግራምም ይህን ታሳቢ እንደሚያደርግ እና ሰብዓዊ ቀውስ ላለባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የልማት ፕሮግራሙ ሴቶችን፣ ህጻናትን፣ ልጃገረዶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን አካታችና ተደራሽ ሊያደርግ እና ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሊሆን እንደሚገባ አጽዕኖት ሰጥተዋል።

ለዚህም የነበሩ ስኬታማ አፈጻጸሞችንና ተሞክሮዎችን ከማስፋፋት እና ቅንጅታዊ አሰራርን ከማጠናከርና ጎን ለጎን የሚስተዋሉትን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ስልት መንደፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የግሉን ሴክተር አጋርነትን በማጠናከር እና ተጨማሪ ሀብት በማሰባሰብ ተጋላጭ ዜጎችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት መረባረብ ይገባልም ብለዋል።

የዩኤን ኤፍ ፒ ኤ(UNFPA) ኢትዮጵያ ዳይሬክተር  ሚስተር ኮፊ ኩዋሜ በበኩላቸው ድርጅቱ በስነተዋልዶ ጤናና በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እንዲሁም ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን መከላከል ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ ሲተገብር መቆየቱን ገልጸዋል። በቀጣይም “እያንዳንዱ ሰው ክብር ያለው፣ ጤናማና የተሟላ ህይወት መኖር የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሁላችንም ቁርጠኛ ልንሆን ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።

Please follow and like us: