ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የ2016 የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የ2016 የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የንቅናቄ መድረክ በአድዋ መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል። የ2016 የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ኃሳብ እንደሚከናወን ተገልጿል። መርኃ ግብሩን የሰላም ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የትምህርት ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት መሆኑም ተጠቁሟል።

የዘንድሮው መርኃ ግብር በ14 መስኮች አገልግሎቶች የሚሰጥበት መሆኑ ተገልጿል። የአረንጓዴ አሻራ፣ የማዕድ ማጋራት፣ ትምህርትና የጤና አገልግሎት አቅመ ደካሞችን መደገፍ ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ይገኙበታል። በመርኃ ግብሩ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች እንደሚሳተፉበትና ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ የሚተመን አገልግሎት እንደሚሰጥበት ተጠቁሟል። በመርኃ ግብሩ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም እንዲሁ።  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2016 የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማስጀመራቸው ይታወሳል።

 

Please follow and like us: