ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች በተሟላ እና ዘላቂነት ባለው መልኩ ለመፍታት ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል

ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች በተሟላ እና ዘላቂነት ባለው መልኩ ለመፍታት ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ እታገኘው አሰፋ ገለጹ።

በብሔራዊ የልዩ ድጋፍ አገልግሎት ማዕቀፍ እና የአካቶ ትግበራ መመሪያ ላይ የባለድርሻ አካላት ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ የምክክር መድረክ ተካሂዷል። በመድረኩ የሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ እታገኘው አሰፋ በምክክር መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል “የልዩ ድጋፍ አገልግሎት (Urban Destitute Support)” ፕሮጀክት በመቅረጽ በመንግስትና በዓለም ባንክ በተመደበ በጀት፣ በሴክተሩ አስተባባሪነትና በተመረጡ ከተሞች እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ ከሚሰሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋርም ውል በመግባት ዜጎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው እራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ካለው ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር እና ከችግሮቻቸው ግዝፈት እንዲሁም ወደፊትም ሊፈጠሩ የሚችሉ ተመሳሳይ ሁኔታዎች አንጻር እየተተገበረ ባለው ፕሮጀክት ብቻ ችግሩን በተሟላ አኳሃን መፍታት አዳጋች እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ጠንካራ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ይገባል ያሉት ወ/ሮ እታገኘው፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዓለም ባንክ በተመደበ በጀት አማካሪ ድርጅት በመቅጠር የብሔራዊ ልዩ ድጋፍ አገልግሎት ማዕቀፍ (National Urban Destitute Support Framework) መዘጋጀቱን አንስተዋል። ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ጉዳዮች ተቋማት በእቅዶቻቸው አካተው እንዲተገብሩ ለማድረግ የአካቶ ትግበራ ጋይድ ላይን (National Urban Destitute Support Mainstreaming Guideline) ረቂቅ ሰነድ በተመሳሳይ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

የመድረኩ ዓላማም የአሰራር ማዕቀፎቹ ወደ ትግበራ ከመሸጋገራቸው በፊት ባለድርሻ አካላት ሙያዊ ግብዓት እንዲሰጡበት ለማስቻል ያለመ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም እንደሀገር ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር በተሟላ እና ዘላቂነት ባለው መልኩ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንዲቻል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሚናቸወን ሊወጡ ይገባል ብለዋል። በምክክር መድረኩ ከፌደራል፣ ከክልሎች፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ከልማት አጋር ድርጅቶች የተውጣጡ ተገኝተዋል። በ2007 ዓ.ም የፀደቀውን ብሄራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ እና በ2008 ዓ.ም የተዘጋጀው የማስፈጸሚያ ስትራቴጂን መሰረት በማድረግ የገጠር እና የከተሞች የልማታዊ ሴፍኔት ፕሮግራሞች ተቀርጿል፤ አሁን ላይም ሁለተኛው ምዕራፍ በመተግበር ላይ ይገኛል።

 

Please follow and like us: