በክልሎችና የፌደራል ተቋማት መካከል ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር የዜጎችን ህገወጥ ስደት በዘላቂነት መከላከል ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

በክልሎችና የፌደራል ተቋማት መካከል ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር የዜጎችን ህገወጥ ስደት በዘላቂነት መከላከል እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤት ዓመታዊ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት፥ ኢትዮጵያ የፍልሰተኞች መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ሀገር በመሆኗ ጫናዎች እንዳሉባት አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የውጭ ፍልሰተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመቀበል ተገቢውን ከለላና ጥበቃ እያደረገች ነው ብለዋል።በአንፃሩ ዜጎቿ በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች በሰው የመነገድና በህገወጥ መንገድ ደንበር የማሻገር ድርጊት ሰለባ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህ የወንጀል ቡድኖች በሰው ልጅ እና በሀገራት ደህንነት ስጋት መፍጠራቸውን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያም የዚህ ስጋት ካለባቸው ሀገራት አንዷ መሆኗን አንስተዋል። በመሆኑም የፍልሰተኞችን ሰብዓዊ መብትና የሀገርን ብሔራዊ ደህንነት ማስጠበቅ የሁሉም ስራ መሆኑን ተናግረዋል። በምክክር መድረኩ የኢትዮጵያ የፍልሰት አስተዳደር የህግ እና ተቋማዊ ማዕቀፎች፣ ከሳዑዲና ሌሎች ሀገራት ተመላሾችን በመተለከተ እስካሁን የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው፥ የፍልሰት ጉዳይ ቁልፍ ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዜጎች ለህገወጥ ስደት የሚዳረጉት ከድህነት ባለመውጣታችን ነው ብለዋል። ችግሩን ለመቀነስ በሁሉም ዘርፍ ራሰን ለመቻል የተጀመሩ ሀገራዊ ትልሞችን ማፋጠን እና የስራ ዕድልን ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ክልሉም ሚናውን በአግባቡ ይወጣል ብለዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፥ ከስደት ተመላሽ ዜጎች ዳግም በህገ ወጥ መንገድ እንዳይሰደዱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ህግን ማስፈጸምና የድንበር ቁጥጥር ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንዳሉት፥ የፍልሰት እና የዜጎች ጉዳይ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ትብብርን ከሚጠይቁ ዋና አጀንዳዎች እየሆነ መጥቷል። ኢትዮጵያ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰው፥ በሀገር ውስጥ በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር አለመዳበሩ በዲፕሎማሲ ስራዎች ላይ ጭምር ጫና እየፈጠረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና የራሷን ህጎች በመተግበር የፍልሰት አስተዳደርን ለማዘመን ጥረት ላይ ናት ብለዋል። ህገወጥ ፍልሰትን ለመከላከል እስከ ታችኛው መዋቅር መናበብን ይሻል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ የተጀመሩ እርምጃዎች መጠናከር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሰጡት ማጠቃለያ ክልሎች የዜጎችን ህገወጥ ፍልሰት ለመከላከል ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል። ከዚህ አኳያ በክልሎችና የፌደራል ተቋማት መካከል ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር ሊፈጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ ኢትዮጵያውያን እንዳይሰደዱና ጉዳት እንዳይደርስባቸው ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ስራ ይጠይቃል ነው ያሉት። ለዚህም በሌማት ትሩፋት፣ በበጋ መስኖና በሌሎችም የልማት መስኮች ሀገራዊ እድገትን ማፋጠን፣ የስራ ዕድል ፈጠራን ማስፋት፣ ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን መከተል እንደሚገባ ተናግረዋል። ለዚህም ብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤቱን ማጠናከር እና ክልሎችም በተዋረድ እንዲሰሩ ማድረግ ወሳኝ ነው ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Please follow and like us: