በማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው ደሃና ተጋላጭ ተብለው የተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል

የ2016 በጀት ዓመት የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት የቋሚና ቀጥታ ዘርፍ ትግበራ አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ የሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ ባደረጉት ንግግር፥ የኢፌዴሪ መንግስት የፍትህ፣ የገንዘብ፣ የጉልበት ወይም የጤና ሁኔታዎች የገደባቸው እና በማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው ደሃና ተጋላጭ ተብለው የተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየሰራ ይገኛል። በተለይ በገጠር ያሉ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች ከድህነት እንዲወጡ እና ራሳቸውን ከመቻል በዘለለም በሃገር ግንባታ ሂደት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዲችሉ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተገበረ ይገኛል ብለዋል፡፡ ለዚህም ክልሎችን፣ የከተማ አስተዳደሮችን እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በማስተባበር በፕሮጀክቱ የታቀፉ ወገኖች የቋሚና የቀጥታ ድጋፍ እንዲያገኙ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል። በማህበራዊ ሰራተኞች አማካኝነት በሚደረግ የቤት ለቤት ጉብኝትና በኬዝ ማኔጅመንት መረጃዎች በመታገዝም ባለፉት አመታት በርካቶችን የጤና፣ የገንዘብ፣ የእህል እና የአይነት ድጋፍ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አማካሪ አቶ ፈለቀ ጀምበር በበኩላቸው ዜጎችን የተሻለ ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ሴክተሩ ትልቅ ተቋማዊ ሃላፊነት የተጠላበት መሆኑን ገልጸው፥ የፕሮግራሙ አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ በየጊዜው በመገምገም ያጋጠሙ ችግሮችን በዘላቂነት እየቀረፉ መሄድ ይገባል ብለዋል። በመሆኑም ጠንካራ አፈጻጸም ካላቸው ክልሎች ትምህርት በመውሰድ በቀጣዩ አመት በሚኖረው የፕሮግራሙ ትግበራ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ሁሉም የድርሻቸውን እንዲወጣ በአጽዕኖት አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ በሀገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የ2016 ዓ.ም በገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል።

በትግበራ ሂደት የተገኙ ተሞክሮዎችን አስመልክቶ ልምድ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን ባጋጠሙ ችግሮች፣ በተወሰዱ መፍትሄዎችና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ዙሪያም በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። በመድረኩ የክልልና የከተማ አስተዳደር የፕሮግራሙ አስተግባሪዎች ተገኝተዋል።

 

Please follow and like us: