በዘንድሮ የወሰን ተሻጋሪ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሳተፉ ወጣቶች ኦረንቴሽን እና ስልጠና ተሰጥቷል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሙና አህመድ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያለማንም ቀስቃሽ የሚሰራና በምትኩም ምላሽ የማይጠበቅበት የህሊና እርካታ የሚሰጥ ሰናይ ተግባር ነው።

በጎነትን ለማስረጽ፣ የአብሮነት እሴቶችን ለማጎልበት፣ ሰላምን ለማጽናት፣ ቀጣይነት ያለውና አስተማማኝ ልማትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ጠንካራ ሀገረ መንግስትን ለመገንባትና ወደ ቀደመ ከፍታዋ ለመመለስ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ መነሻነት የዘንድሮ ወሰን ተሻጋሪ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል ለ3ኛ ጊዜ በ14 የስምሪት መስኮች በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንደሚካሄድ ጠቁመው ለተቀደሰው ዓላማ የተሰባሰቡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችንም አበረታተዋል።

አፈጻጸሙ በተመለከተም የክትትልና ድጋፍ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። ወጣቶቹ በሚኖራቸው ቆይታም ስነምግባርን በመላበስ የአካባቢያቸውን ባህል እንዲያስተዋውቁና ከሌሎችም እንዲማሩ፣ እንዲሁም የአብሮነት እሴትን ማጎልበት፣ የሀገርና የትውልድ ግንባታን ማጠናከርና የዜጎችን ተሳታፊነትንና ተጠቃሚነትን ማሳደግ የሚያስችሉ በጎ ስራዎችን በማከናወን ህዝብና ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉና ዓላማው እንዲሳካ የድርሻቸውን እንደወጡ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ አደራ ብለዋል።

ዘንድሮ በሚካሄደው ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሁሉም ክልል የተውጣጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይም ኦረንቴሽንና ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል።

 

Please follow and like us: