በተፈጥሮና ሰው ሰራሸ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ እና መሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት እየተገበረ ይገኛል

በትግራይ ክልል በተፈጥሮና ሰው ሰራሸ ምክንያት በግለሰብና በማህበረሰብ ደረጃ ለደረሰው የአእምሮ ጤና፣ የስነልቦና እና ማህበራዊ ጉዳት የተቀናጀ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

በስልጠና መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ ባደረጉት ንግግር፤ በአገራችን በተፈጥሮና ሰው ሰራሸ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ እና መሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅም ለማሳደግ እንዲያስችል (Response – Recovery – Resilience for Conflict Affected Communities in Ethiopia (3R-4-CACE) Project) ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተገበረ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

እንደሀገር በተፈጥሮና ሰው ሰራሸ ምክንያት ለፆታዊ ጥቃት የተጋለጡ ሴቶችና ህፃናትን መደገፍ ላይ ትኩረት ያደረገው የፕሮጀክቱ ክፍል በሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚመራ እና በአሁኑ ወቅትም ፕሮጀክቱን በሙሉ አቅም ተግባራዊና ውጤታማ ለማድረግ ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ጋር በመተባበር ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ስልጠናው የፕሮጀክቱ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም ትግራይን ጨምሮ ግጭት በተከሰተባቸው የአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ለባለሙያዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በተለያየ ዙር የአሰልጣኞች ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል። ይህም ስልጠና በክልሉ በማህበራዊ ሴክተር የሚሰሩ ባለሙያዎች የተቀናጀና ሁለገብ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸውን አቅም በማጎልበት እስከታች እንዲያወርዱ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይም በክልሉ ለሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማነት አስፈላጊውን እገዛ እና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ እና መልሶ ማቋቋም ቢሮ ኃላፊ ክብርት ጀነራል ዘውዱ ኪሮስ በበኩላቸው ስልጠናው በዘርፉ የሚታየውን የእውቀትና ክህሎት ክፍተት በመሙላት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በእውቀት ላይ የተመሠረተ የተቀናጀ የማህበረ – ስነልቦናዊ ድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸው ሰልጣኞች በአግባቡ በመከታተል በስራ ላይ እንዲያውሉ በአጽዕኖት አሳስበዋል።

Please follow and like us: