ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ በሰላም ግንባታ እና በአረንጓዴ አሻራ ላይ ያተኮሩ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛል።

(አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም) የኢፌዲሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከማዕከላዊ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሰላም ዕሴት ግንባታ እና የአረንጓዴ አሻራ ላይ ያተኮሩ መርሃ-ግብሮችን እያካሄዱ ይገኛል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ እንዳሻው ጣሰው በሆሳዕና ከተማ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ቃል የሩጫ መርሀ ግብሩ አሰጀምረዋል። ሩጫው ሰላምና አብሮነት ለማጠናከር እና ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የማህበረሰብ ንቅናቄ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ለዘላቂ ሰላም ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸው፥ ቀጣይና አሰተማማኝ ሰላም በመገንባት ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ ወጣቶቹ በዕለቱ” የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ በሚል በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የተጀመረውና የአረንጓዴ አሻራ አካል የሆነውን ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በሀድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ አከናውነዋል። የችግኝ ተከላውን ያስጀመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ምክትልና ቢሮ እና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተመስገን ሀይሌ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የተያዘው ግብ እንዲሳካ ወጣቱ ሚናውን መወጣት እንዳለው ገልጸዋል።

መንግስት በሁሉም ዘርፍ በትኩረት እየሠራ ለሚገኘው ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ወጣቶቹ እየሰጡ ለሚገኘው አዎንታዊ ምላሽ አቶ ተመስገን አመስግነዋል። አክለውም ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶችን ለበጎ ዓላማ በማስተሳሰር ለሰላም ግንባታ የማይተካ ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል።

በመርሃ – ግብሩ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተጀመሩ ሰራዎችን ለማስቀጠል እንዲያስችል የተዘጋጀውን አርማና ባንዲራ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አበርክቷል።

Please follow and like us: