ኢትዮጵያ እና አየርላንድ 30ኛ ዓመት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አከበሩ

ኢትዮጵያ እና አየርላንድ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን 30ኛ ዓመት አክብረዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የአየርላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የመከላከያ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ሚሼል ማርቲን እና የሀገሪቱ ከፍተኛ ልዑክ ቡድን ገኝተዋል። የኢትዮጵያን መንግስት ወክለው ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘላቂ ወዳጅነት የገለጹ ሲሆን በቀጣይም ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመፍጠር ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።

እንደ አጋር በአስቸጋሪ ጊዜያት በአንድነት ቆመናል ያሉት ሚኒስትሯ አየርላንድ ያደረገችውን ​​ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲሁም ዝነኛው አየርላንዳዊው ሙዚቀኛ ቦብ ጌልዶፍ በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለተከሰተው ረሃብ እርዳታ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ ኮንሰርት ማዘጋጀቱን አስታውሰው ምስጋና አቅርበዋል። ሚኒስትሯ የአየርላንድ ኤምባሲ በምርታማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም (PSNP) በኩል ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች በተለይም ለህጻናት፣ ለሴቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ለሚያደርገው ድጋፍ እውቅናና ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት በልማት፣ ጤና ጥበቃ፣ ትምህርት፣ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና የአካባቢን ዘላቂነት ባሉ ጉዳዮች ላይ ትብብርን ለማጠናከር ጠንካራ የፖለቲካ ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅ ገልፀዋል። ከልማት ትብብር ባሻገር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች በትብብር ለመስራት ያለው አቅም ትልቅ ነው ያሉት ዶ/ር ኤርጎጌ ይህንን አጋርነት የበለጠ ለማራዘም በሁለቱም ሀገራት መካከል ቁርጠኝነትን ይጠይቃልም ብለዋል።

ወደፊትም ሁለቱም ሀገራት በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፣ በኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎችን ለማመቻቸት አየርላንድ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ መቀጠል እንደሚገባት ሚኒስትሯ ገልፀዋል። የአየርላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የመከላከያ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚሼል ማርቲን በኩላቸው በንግድ፣ በአቬየሽን፣ በቱሪዝም፣ ለችግር ተጋላጭ ዜጎችን በመደገፍ እና በሌሎችም መስኮች የሁለትዮሸ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

Please follow and like us: