ለሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ስኬታማ ትግበራ የተቋሙ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል – ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ

የተቋሙ ባለሙያዎች በሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ በመጨበጥ ለስኬታማ ትግበራ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ዙሪያ የተቋሙ ባለሙያዎችን አቅምና ሚና ለማጎልበት ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና አዘጋጅቷል። በስልጠናው መርሃ ግብሩ ላይ ሚኒስትር ዴኤታዋ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ባደረጉት ንግግር፥ ባለፋት ጊዜያት የተከሰተውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ የተፈጠሩ አለመግባባቶች እና ግጭቶች በሀገርና በዜጎች ላይ ጉዳት ማስከተሉን ገልጸዋል።

ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ጾታዊ፣ አካላዊ፣ አእምሯዊና ስነልቦናዊ ጥቃት መፈጸሙንና ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸውን አስታውሰዋል። ሁኔታው በህብረተሰቡ ዘንድ ቂሞችና መቃቃሮች እንዲፈጠሩ ከማድረጉም በላይ በማህበራዊ ትስስሩ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡ የደረሰውን ሁለንተናዊ ጉዳት ለማከም የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም መንግስት በእርቅ እና ፍትህ አማራጮች የተፈጠሩ ቁርሾና በደሎችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቱንም ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ብለዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በልዩ ሁኔታ መታየት የሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ደግሞ ከሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ጋር በተያያዘ የፖሊሲውን አፈፃፀም የመከታተልና የማስተባበር ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሽግግር ፍትህ ሂደቱ ተሳትፎን የማረጋገጥ፣ ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ የድርጊት መርሃ ግብር የመንደፍ፣ በየደረጃው አደረጃጀቶችና መዋቅር የመፍጠር፣ ማህበራዊ ለውጦችን የማጠናከር ብሎም ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑንም አስገንዝበዋል። በመሆኑም ፖሊሲውን በማስተግበር ረገድም ሆነ ለተቋሙ በተሰጠው ተልዕኮ ዙሪያ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች የጠራ ግንዛቤ በመጨበጥ ለስኬታማ አፈጻጸም የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታዋ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምከትል ኃላፊ ሚስተር ቻርልስ ኪዌሞይ በበኩላቸው ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰጡ ኃላፊነት በፖሊሲው ማስፈጸሚያ ፍኖተ ካርታ ላይ በዝርዝር መመላከቱን ጠቁመው ኮሚሽኑ በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል። ስልጠናው በፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች አማካኝነት የተሰጠ ሲሆን በፓሊሲው ዙሪያ ግልፅነትና ማብራሪያ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አካላት ሙያዊ ምላሽ ተሰጥቶበታል።

በስልጠናው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

Please follow and like us: