በኢትዮጵያ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት እገዛ ይደረጋል – የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ

(አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16/ 2016 ዓ.ም) በኢትዮጵያ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት አስፈላጊው እገዛ የሚደረግ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ ገለጹ።

በተለያዩ የሙያ መስኮችና የኃላፊነት ደረጃዎች የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል። በሁሉም ዘርፍ ማብቃትና የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ፤ በኢትዮጵያ በሥርዓተ-ፆታ እኩልነትና የሴቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶችን አድንቀዋል።በተለይም በተለያዩ የአመራርነት ደረጃዎች የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ የሚታዩ ለውጦች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በትምህርት ሽፋንና ተደራሽነት፣ በጤና አገልግሎት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎችም መስኮች ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውን አንስተዋል። በመሆኑም በተለያዩ የሙያ መስኮችና የኃላፊነት ደረጃዎች የሴቶችን ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶችን አድንቀው፤ በዚህ ረገድ የመንግሥታቱ ድርጅት እገዛና ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በሁሉም የሙያ መስኮችና የኃላፊነት ደረጃዎች የሴቶችን ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ የመንግሥት ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠው፤ የሚታዩትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍና ሴቶችን ለማብቃት የሁሉም አካላት ድጋፍና እገዛ አስፈላጊ ስለመሆኑም አጽዕኖት ሰጥተዋል።

Please follow and like us: