የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በአመራር አቅም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኛ ዜጎች አቅም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ ብቁና ተወዳዳሪ አመራሮችን ለማፍራት እንደሚያስችል ተጠቁሟል። ስምምነቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ዛዲግ አብርሃ በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል። በስምምነት ስነስርዓቱ ላይ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኛ ዜጎችን መብት ለማስከበር፣ በየዘርፉ ያላቸውን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና በየደረጃው ለማብቃት ከተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል። ሀገር ማለት ሰው ነው።

ሀገርን ለመለወጥ የሰው ሀይል ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም ከአካዳሚው ጋር በጋራ በመሆን በፌዴራልና በክልል የሚገኙ ሴት አመራሮችን ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል። ይህም የአስፈጻሚ አካላትን አቅም በመገንባት የአፍሪካ የብለፅግና ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአመራር ብቃት ያላቸውና የመሪነት ሚና የሚጫወቱ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኛ ዜጎችን ለማፍራት ያለመ ስምምነት መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ትልቅ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው ስምምነት ወደ ተግባር እንዲሸጋገር እና ስኬታማ እንዲሆን ትኩረት ሰጥቶ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው አካዳሚው አቅምን ለመገንባት የሚያስችሉ የአመራር ልማት ፕሮግራም፣ የአመራር የልህቀት ሽልማት፣ የመሠረተ ልማት እና የጋራ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የአቅም ግንባታ ስልጠናዎቹ እንደሀገር የሚስተዋለውን የአመራር ክፍተት ለመሙላት እና በተለይ ተተኪ ወጣት አመራሮችን ለማፍራት ያግዛል ብለዋል።

Please follow and like us: