በሀገራዊ ልማትና በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ የሴቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል – ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

በሀገራዊ ልማትና በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ የሴቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ። ሚኒስትሯ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጥና ተደራሽ በሆነ መልኩ የሚሰጥበትን ሁኔታ መፍጠር የተቋማቸው አንዱና ዋነኛ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ በመዘጋጀቱ አገልግሎቱ በተሻለ መልኩ እንዲሰጥ ለማድረግ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል። የፖሊሲው እውን መሆን በተለይም ሴቶች በበጎ ፈቃድና በሌሎች የማህበረሰብ አገልግሎቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑንም አስረድተዋል። በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ከ24 ሚሊየን በላይ ወጣቶች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሀገራዊ ልማትና በበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ የሴቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ሚኒስትሯ ጨምረው ተናግረዋል። ከአረንጓዴ አሻራ በተጨማሪ በሌማት ትሩፋትም የሴቶች ተሳትፎ ማደጉንና እያስመዘገቡ ያለው ውጤት አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Please follow and like us: