የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለህይወት ስንቅ የሚሆን መልካም ተግባር የሚከወንበት መስክ ነው – ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለህይወት ስንቅ የሚሆን መልካም ተግባር የሚከወንበት መስክ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ ገለጹ፡፡

በጎ ፈቃደኝነት ዜጎች ያለማንም ቀስቃሽ በሰብዓዊነት በመነሳሳት ማህበረሰባቸውን ለማገልገል የሚያከናውኑት ተግባር ነው፡፡ በሀገራችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ወጣቶችን ከመሳብ ባለፈ ተግባሩ ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡ ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ የሆነው ወሰን ተሻጋሪ ሰብዓዊ ተግባር ደግሞ ከሚሰጠው አገልግሎት ባለፈ አብሮነትንና ሰላምን በማጽናት የባህልና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ መሰረት እየሆነ መጥቷል፡፡ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

አገልግሎቱ መሠጠት ከተጀመረበት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የበጎ ፈቃደኞች ቁጥር እያደገ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታዋ ፕሮግራሙ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣችን ከማነቃቃት ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን፣ አብሮነትንና ሰላምን የሚያጠናክር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ መርሀ ግብሩ የአካባቢን ባህል እና ወግ ከመለዋወጥ ባለፈ ለህይወት ስንቅ የሚሆን መልካም ተግባር የሚከወንበት መሆኑንም ጠቁመዋል። በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀ ግብርም 21 ሚሊዮን ወጣቶች በ14 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው ማህበረሰባቸውን የሚጠቅም ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተዘዋወሩባቸው የክልል ከተሞች ያገኙት የማህበረሰቡ እንግዳ አቀባበልና የወጣቶች ተሳትፎ እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል፡፡ ከሀላባ ዞን የመጣው ወጣት ኑረዲን ሚስባህ በጎነት ለራስና ለሀገር የሚሰራ ሰብዓዊ ተግባር መሆኑን በመናገር ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ደግሞ ሌሎች ወጣቶች ተግባሩን እንዲቀላቀሉ ያነሳሳቸዋል ብሏል፡፡ ወጣቶቹ በአጠቃላይ በተንቀሳቀሱባቸው የክልል ከተሞች የደም ልገሳ፣ የችግኝ ተከላ፣ የአረጋውያን ቤት እድሳትና ሌሎች በጎ ተግባራትን ማከወናቸውን ተናግረዋል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት ለራስ ደስታና የህሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑን የገለጸችው ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የመጣችው ወጣት ሊሊ ተስፋዬ ናት፡፡

በአካባቢዋ ወጣቶችን በማስተባበር በደም ልገሳ እና አረጋውያንና ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን በመንከባከብ ስትሳተፍ እንደነበር ገልጻለች፡፡ በቀጣይም ይህንኑ ተግባር በራሷ አቅም እንድታከናወን መነሳሳት እንደፈጠረላት ተናግራለች፡፡ ከአፋር ክልል የመጣችው ወጣት ሀናን መሀመድ በበኩሏ፤ በአካባቢዋ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማህበር በማቋቋም በቋሚነት 40 አረጋውያንን እየረዱ እንደሚገኙ ጠቁማለች፡፡ በተጨማሪም ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስና የአልባሳት ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጻለች፡፡ “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለሶስተኛ ጊዜ በተከናወነው የዘንድሮው ወሰን ተሻጋሪ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወጣቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል፡፡

Please follow and like us: