ለሀገራዊና ዓለም-አቀፋዊ ተግዳሮቶች ወጣቶች የተለያዩ የዲጂታል ፕላትፎርሞችን በመጠቀምና መፍትሄዎችን የሚያመላክቱ መተግበሪያዎችን በመፍጠር ረገድ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ ክብርት ሙና አህመድ

የአለም የወጣቶች ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ እንደገለፁት ወጣቶች የተለያዩ የዲጂታል ፕላትፎርሞችን በመጠቀም ለሀገራዊና ዓለም-ዓቀፋዊ ተግዳሮቶች መፍትሄዎችን የሚያመላክቱ የፈጠራ ስራዎችን /መተግበሪያዎችን በመፍጠር ረገድ ግንባር ቀደም መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ሚኒስትር ድኤታዋ እንደገለፁት በኢትዮጵያ ወጣቶች ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል የሚሸፍኑ እንደመሆኑ አገራችን የጀመረችው የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግ ወጣቱን ትውልድ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማብቃት ስራ ፈጣሪና ተወዳዳሪ ዜጋን ማፍራት ለነገ የማይተው ጉዳይ ነው፡፡ አክለውም የዘንድሮ የዓለም የወጣቶች ቀንን በሀገራችን “ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ማብቃት ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት” በሚል መሪ-ቃል ማክበር ያስፈለገበት ዓቢይ ምክንያት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለዘላቂ ልማት፣ የዓለማችንንና የሀገራችንን የወደፊት ሁኔታን በመቅረፅ እና ወጣቶቻችን ይህንን ለውጥ እንዲመሩ በማስቻል ረገድ የሚጫወተው ሚና ወሳኝ በመሆኑ ነው ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደገለፁት ቴክኖሎጅን በመጠቀም የፈጠራ ችሎታን ማዳበርና ምቹ ምህዳርን በመፍጠር የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፎች፣ የማማከር እና የስልጠና መርሃ-ግብሮችን በማመቻቸት ጥረታቸውን ለማገዝ በየዘርፉ ምህዳሩን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል ። የዘንድሮ የአለም የወጣቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ24ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ “From Clicks to Progress: Youth Digital Pathways for Sustainable Development” “ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ማብቃት ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት” በሚል ሀገራዊ መሪ-ቃል ነሀሴ 6 ይከበራል ።

Please follow and like us: