በስርዓተ ፆታ እኩልነት፣ በአረንጓዴ ልማት እና በሌሎችም መስኮች ከአረንጓዴ ልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (GGGI) ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (GGGI) ተወካይ ሚስተር ዳንኤል ኦግቦናያ እና ልዑካን ቡድናቸውን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የስራ ኃላፊዎቹ በአረንጓዴ ልማት መርሀ ግብር፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በስርዓተ ፆታ እኩልነት፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት፣ ወጣቶችንና አካል ጉዳተኞችን አካታች ባደረጉ ተግባራት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያሰችል ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል። በዚሁ ወቅትም፥ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሴቶች፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞች ይበልጥ ተጎጂዎች መሆናቸውን ገልፀዋል። የአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል እና የዜጎችን ማህበራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን በሰፊው አብራርተዋል። የአረንጓዴ ልማት ተግባራት ከአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ እና ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራሞች መካከል አንዱ መስክ መሆኑን ክብርት ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ በየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች፣ ታዳጊ ህጻናትና ወጣቶች በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙና ወጤቱንም በተጨባጭ መመልከት መቻሉን አስረድተዋል። በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር እንዲሁ ሴቶች በስፋት እየተሳተፉ መሆኑንና በዚህም የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን ጨምረው ገልጸዋል። እንደሀገር የሚካሄዱ ሌሎች ሰፋፊ ኢንሼቲቮች መኖራቸውን ክብርት ሚኒስትሯ ገልጸው የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከልና በመቋቋም፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ በማብቃት እንዲሁም ወጣቶችንና አካል ጉዳተኞችን አካታችና ዘላቂነት የሆኑ ተግባራትን ከGGGI ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (GGGI) ተወካይ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየዘርፉ እየሰራቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል። በቀጣይም በተጠቀሱት መስኮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያግዝ ፕሮጀክት በማዘጋጀት በስራ ላይ እንዲውልና ስኬታማ እንዲሆን GGGI አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በውይይቱ ወቅት አስታውቀዋል።

Please follow and like us: