ስምምነቱ ሰብዓዊ መብትን፣ የስርዓተ ጾታ እኩልነትንና ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ ያለንን ቀርጠኝነት ማሳያ ነው – ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የምስራቅ አፍሪካ የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሴቶችና አካል ጉዳተኛ መብትና ጥበቃ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ያለመ ስምምነት ተፈራረሙ።

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ ሰብዓዊ ቀውስ በሚከሰትበት ወቅት በተለይ ሴቶች፣ ልጃገረዶች፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ለአስከፊ ችግር ሊገለጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል። በተለይ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ ማህበራዊ መገለልና የመሠረታዊ አገልግሎት ተደራሽነት አናሳ መሆን በእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አንስተዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሀገር ለአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ሁሉን አቀፍ የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ፣ የህጻናት መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የሴቶችና ወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ሆኖም ፍትህና ርትዕን እውን ለማድረግ ብሎም በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ የሁሉንም አካላት ትብብርና ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ይህ የትብብር ማዕቀፍም የሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ተጋላጭ ዜጎችን ሰብዓዊ መብትና ሁለንተናዊ ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የስርዓተ ጾታ እኩልነትንና ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ ያለንን ቀርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የህግ የበላይነትን፣ እኩልነትንና የተጠያቂነት ስርዓትን ለማስፈን እንዲሁም የአለም አቀፍ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደፍኖተ ካርታ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል። ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ጠቁመው እስካሁን ተመድ እያደረገ ላለው ድጋፍም ክብርት ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል። በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካይ ሚስተር ማርሴል ክሌመንታኮሆፎ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር እየወሰደ ያለው እርምጃ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል። ማዕቀፉ ሰብዓዊ መብትን ለማስጠበቅ እና ተጠያቂነት ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል። ለስምምነቱ ስኬታማ ትግበራም ተመድ በትኩረት እንደሚሰራና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተወካዩ አረጋግጠዋል። ስምምነቱ ለሶስት አመታት እንደሚቆይና የአቅም ግንባታ፣ የስርዓት ዝርጋታ እንዲሁም የግንዛቤና የንቅናቄ ስራዎችም የስምምነቱ ዋነኛ አካል መሆናቸው ተገልጿል። በቀጣይ በተጠቀሱት በዘርፎች የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከርና ውጤታማ ለማድረግ በትብብር እንደሚሰሩ የስራ ኃላፊዎቹ ተስማምተዋል። በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ተቋማት ትብብር ብሔራዊ የሴቶች መብት ጥበቃ ጋይድላይን እና የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት መጀመሩን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Please follow and like us: