በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሁላችንም ርብርብ እና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችንና ጎጂ ልማዳዊ ለመከላከል የሁላችንም ርብርብ እና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉደይ ሚንስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

በብሔራዊ ጥምረት የሴት ልጅ ግርዛትና የልጅነት ጋብቻ በመከላከል ዙርያ ለተገኘው ውጤት የእውቅና መስጫ መርሀ ግብር ተካሂዷል። መርሀ ግብሩ ላይ ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተሰፋዬ፤ በተቀናጀ ጥረት በርካታ ህጻናትንና አፍላ ወጣት ሴቶችን ከአሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ወንጀል መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡ ይህ ዘርፈ ብዙ ጥምረትና ስኬት ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን ጠቁመው በትብብር መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ እንደሀገር ድርጊቱን ለመከላከል የሚያስችል ህግ ወጥቶ በስራ ላይ የዋለ ቢሆንም የተዛባ የስርዓተ ጾታ ግንኙነት፣ የተናጠል ጥረታችንና ቁርጠኝነታችን በሚፈለገው ደረጃ ከፍ ባለማለቱ የተነሳ ሴቶችና ህጻናት አሁንም የጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና የጥቃት ሰለባ ሆነው ቀጥለዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ዛሬም የፍትህ አካላትን ጠንካራ እርምጃ፣ የጤናና የትምህርት ሴክተሩን ርብርብ፣ የሃይማኖት አባቶችን ቁርጠኝነት እና አንቀሳቃሽነት እንፈልጋለን ብለዋል። በጥምረቱ ስኬት ዓለም አቀፍ እውቅና በመገኘቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የማኅበራዊ ልማት፣ የጤና፣ የባሕል እና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ ይህ ዓለም አቀፍ እውቅና በቅንጅት መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።

ያለ ዕድሜ ጋብቻን እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረትም ሁላችንም ኀላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ሲሉ በመድረኩ ተናግረዋል። የተባበሩት መንግስታት ረዳት ሴክሬተሪ ጀነራል እና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ዶ/ር ራሚዝ አልካባሮቭ እውቅናው ትልቅ ሽልማት መሆኑን ጠቁመው ወደፊትም ኢትዮጵያ ድርጊቱን ለማስቆም የምታደርገው ጥረት እንዲሳካ አስፈላጊው ተመድ እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ለማስቆም የተቋቋመው የጥምረቱ የስራ እንቅስቃሴ አምስተኛው ዓመት ላይ መድረሱን በመድረኩ ተገልጿል።

Please follow and like us: