በየዘርፉ የሚጨበጥ ውጤት በማምጣት በሴክተሩ ተደራሽ የሆኑትን የማህበረሰብ ክፍሎች ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ ሁሉም በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል – ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የሴክተር ጉባኤ ተጠናቋል።

የጉባኤው መጠናቀቅን ተከትሎም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የስራ መመሪያና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በዚህም መሠረት በ2017 ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በየክልሉ በየዘርፋ ያለውን አሁናዊ ነባራዊ ሁኔታ ለመገንዘብ የሚረዳ ችግር ፈቺ ጥናት ማካሄድና መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል። በየደረጃው የሚገኙ አሰፈፃሚ አካላት ሊቆጠሩ እንዲሁም ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም አደራ ብለዋል።

በየአካባቢው ያሉ አጋር ድርጅቶችን በመለየት በገቡት የስራ ውል ስምምነት መሠረት እየተገበሩ መሆኑን መመዘንና መከታተል እንደሚገባ አንስተዋል። በተመሳሳይ የተቋማት አካቶ ትግበራን ለመመዘን የሚያግዙ የአሰራር ማዕቀፎች በስራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግና ተጠያቂነትን ለማስፈን በትኩረት መሠራት እንዳለበትም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በሌላ በኩል በቀጣዩ አመት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀም ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል የተቋቋመውን ጥምረት ለማጠናከር፣ የህፃናት መልሶ ማቀላቀልና ማዋሃድ ፕሮግራም ለመተግበር እንዲሁም በ2017 ዓ.ም የሴክተር ዕቅድ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ተፈራርመዋል። እንደ አጠቃላይ እነዚህን ተግባራትን ጨምሮ በየዘርፉ የሚጨበጥ ውጤት በማምጣት በሴክተሩ ተደራሽ የሆኑትን የማህበረሰብ ክፍሎች ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ ሁሉም በቁርጠኝነት እንዲሰራ ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በአፅንኦት አሳስበዋል።

k

Please follow and like us: