የፆታዊ ጥቃት መከላከል እና ምላሽ አሰጣጥን ውጤታማነት ለማሳደግና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የተዘጋጀ የአሰራር ማዕቀፍን የተመለከተ ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፆታዊ ጥቃት መከላከል እና ምላሽ አሰጣጥን ውጤታማነት ለማሳደግና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል እንዲያስችል የተዘጋጀ የአሰራር ማዕቀፍ ላይ ያተኮረ የስልጠና መድረክ ከጋምቤላ፣ደቡብ ምዕራብ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ለተውጣጡ የዞን መምሪያ ኃላፊዎችና ለአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለሙያዎች በመሰጠት ላይ ይገኛል።

በስልጠናው ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ሰለሞን አስፋው በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ህፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ አማካሪ እንደገለፁት የጥቃት የአፈፃፀም ሂደት በባህሪው ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ ሴቶችና ህፃናት ለከፋ አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ወሲባዊ እንዲሁም ሌሎች ከጤና፣ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጋር ለተያያዙና ለተራዘሙ ተጨማሪ ጉዳቶች ተጋላጭ እያደረጋቸው እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

አቶ ሰለሞን እንደገለፁት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፌዴራል፣ ከክልሎችና ሌሎች ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል፣ ተጋላጭነት ለመቀነስና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በተለይ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ወገኖች የተሟላ፣ ፈጣንና የተቀናጀ አገልግሎት እንዲያገኙና በአገልግሎት ሰጪ አካላትም እንግልት እንዳይደርስባቸው ለማስቻል ብሎም ሴቶችና ህጻናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማበረታታት እንዲሁም የወንጀል ምርመራና የፍትህ ሂደቱን የተሳለጠና ስኬታማ ለማድረግ ያለመ የአንድ ማዕከል፣ ጊዜያዊ የሴቶች ማረፊያና የሴቶች የተሃድሶ ማዕከል ማቋቋምና ተደራሽነቱንም ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንዳለ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ በጾታዊ ጥቃት መከላከልና ምላሽ ስራዎች ወጥ የሆነ ሀገራዊ የአሰራር ስርዓት ባለመኖሩና ጥራቱን የጠበቀ ባለመሆኑ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን ችግር ለመቅረፍ የጾታዊ ጥቃት መከላከልና ምላሽ ሀገር አቀፍ የአሰራር ስርዓት (National GBV SOP) ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ማዘጋጀቱን ጨምረው ገልፀዋል ። የአሰራር ማዕቀፉ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለመከላከል፣ ተጋላጭነት ለመቀነስና ጥራቱን የጠበቀ የምላሽ ስራዎችን ለማከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት መከተል ያለባቸውን የአሰራር ስርዓት የያዘ ነዉ።

 

Please follow and like us: