በስርዓተ ፆታ አካቶ ትግበራ የተሻለ አፈፃፀም ላመጡ ተቋማት እውቅና ተሰጠ

በስርዓተ ፆታ ጉዳይ ተቋማዊነት መከታተያ፣ መመዘኛና ደረጃ መለያ ማዕቀፍ (leveling tool) መሠረት የተሻለ አፈፃፀም ላመጡ ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ሌሎች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ውስብስብ ችግር የመፍታት ተግባር ውስን ለሆኑ አካላት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም አካላት ልዩ ትኩረት፣ ቁርጠኝነት እና ቅንጅታዊ አሰራር ይጠይቃል። የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሰረት ሁሉም ተቋማት በሚያዘጋጇቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ እና ሌሎች የአሰራር ማዕቀፎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅም የሚያስጠብቅና የእኩል እድል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ተደንግጓል ብለዋል፡፡

ሁሉም ተቋማት የሚሰሩት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እስከሆነ ድረሰ አሰራራቸው መፈተሽ፣ አፈፃፀማቸውን መመዘንና ተጠያቂነት ማስፈን ይገባል ብለዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሂደቱን የመደገፍና የማስተባበር ስራ እየሰራ መሆኑንና የስርዓተ-ፆታ ጉዳይ መከታተያ፣ መመዘኛና ደረጃ መለያ ማዕቀፍ (Gender mainstreaming leveling tool) በማዘጋጀት በስራ ላይ ማዋሉን ጠቁመዋል። ምዘናውን ማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያትም የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን በሁሉም ዘርፍ ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማስፈንና የሀገራችንን ራዕይ ለማሳካት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ማዕቀፉ የእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጉዳይ ተፈፃሚነት መመዘን (Inclusive Leveling Tool) በሚችል አግባብ የመከለስ ስራው መጠናቀቁንና የሙከራ ምዘና መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡ የአካቶ ትግበራ የቁጥጥርና ተጠያቂነት ደንብ /Accountability Directive/ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ እነዚህን ሰነዶች ከወጡ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ጋር በተጣጣመና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ወደታች ወርደው እንዲተገበሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በህ/ተ/ም/ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ ወ/ሮ መሠረት ሀይሌ በበኩላቸው በበኩላቸው የዜጎች ፍትሃዊ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ሰላምና ድህንነት ለማስጠበቅ የተጀመረው ጥረት እንዲጠናከርና ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል። በዕለቱ የምዘና ሂደቱ ምን እንደሚመስል በመሪ ስራ አስፈፃሚው በአቶ ከተማ ለገሰ የቀረበ ሲሆን በመደረኩ የተሻለ አፈፃፀም ለስመዘገቡ ጤና፣ ትምህርትና ግብርና ሚኒስቴር እና ድጋፍ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

Please follow and like us: