መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትንና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ተቋማት እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል በተዘጋጀ የ2017 በጀት አመት ረቂቅ እቅድ ላይ ውይይት ተካሂዷል።በመድረኩ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን መከላከል እንዲያስችል የተዘጋጀ የስልጠና ማኑዋል ለባለድርሻ አካላት የበማስተዋወቅ በተሳታፊዎች ግንዛቤ እንዲያዝበት ተደርጓል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ በዚሁ ጊዜ፥ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በየጊዜው በህገወጥ መንገድ ከሀገር ሲወጡ በድበር ጠባቂዎችና ሌሎች የተደራጁ አካላት እጅ እየወደቁ ከፍተኛ ለሆነ የጤና፣ የስነ-ልቦና፣ የአካል ጉዳትና ለሌሎች ተደራራቢ ችግሮች እየተዳረጉ ይገኛል ብለዋል። የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ መንግስት ድርጊቱን ለመከላከል በትኩረት እየሰራ ይገኛል ያሉት ክቡር አቶ ጌታቸው የተለያዩ ተቋማትን ያቀፈ የግንዛቤ ፈጠራ የስራ ቡድን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱንና በተጠናቀቀው በጀት አመትም ሰፋፊ ተግባራት በቅንጅት ሲከናወን መቆየቱን ገልፀዋል።

በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ የወንጀል ድርጊት መሆኑን ለህብረተሰቡ በሰፊው በማስገንዘብ የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል ብለዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ለተመላሽ ዜጎች ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ የመስጠት ብሎም ወደ ቤተሰብ የማቀላቀል ስራ በጋራ መሠራቱን ተናግረዋል። እንዲሁም ፍልሰትን የተመለከተ ሀገራዊ መረጃ ለማደራጀት በጋራ እየሰራ መሆኑንም አያይዘው አንስተዋል።

የመድረኩ ዓላማም በተዘጋጀው እቅድ ዙሪያ በመወያየት ለተሻለ አፈፃፀም ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ እንደሆነ አስረድተዋል፡ በተጨማሪም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል የተዘጋጀው የስልጠና ማኑዋል በስራ ላይ ከመዋሉ በፊት ፈፃሚ አካላት የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መድረኩ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል። በመሆኑም በቀጣይ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና የተጎጂዎችን ሰብአዊ መብት ለማስከበር በሚደረገው አገራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የጥምረቱ አባል ተቋማት የተቀናጀ አገልግሎት እንዲሰጡና ለእቅዱ ስኬታማነትም የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ ጌታቸው በዳኔ ጥሪ አቅርበዋል።

 

Please follow and like us: