ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መነሻቸው የተዛባ የስርዓተ ፆታ አመለካከት ቢሆንም በቀጣይ ከፍርድ ቤቶችና ከሌሎች የፍትህ አካላት ጋር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

የሴቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከሴቶች እና ሕፃናት መብት አያያዞች ጋር በተገናኘ ከአማራ ክልል የክልሉ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች በተገኙበት ውይይት አድርገዋል።

ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መነሻቸው የተዛባ የስርዓተ ጾታ አመለካከት በመሆኑ በሁሉም ደረጃዎች ጥቃቱንና የሚያስከትለውን ጉዳት ትኩረት ተሰጥቶ  እንዳይታይ ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጧል፡፡ በውይይቱም ምንም እንኳን  መንግስት ማህበራዊ ወጎችና ልማዶች በማስወገድ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማስፈንና የሴቶችና ህፃናትን መብት ለማስጠበቅ አለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶችን በመፈረምና ለአፈፃፀማቸው የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎችን በመቅረጽ እየሰራ የሚገኝም  ቢሆንም የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ማረጋገጥም ሆነ የሴቶችና ህፃናት መብትና የፍትህ ተጠቃሚነት እውን ማድረግ  ገና ረጅም ጉዞ የሚጠይቅ መሆኑን ነባራዊ ሁኔታዎች እንደሚያመለክቱ ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም ፆታዊ ጥቃትም ሆነ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ስትራቴጂክ ኃይል የሆኑት የአገራችን ሴቶች በየዘርፉ በሚካሄዱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዳይወጡ፣ ከሚገኘውም ትሩፋት እኩል ተቋዳሽ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሲፈጥር የነገ አገር ተረካቢ ህጻናትንም መፃዒ ተስፋ በማጨለም መድረስ ከሚገባቸው ዓላማ ሳይደርሱ ገና በማለዳው ተሰናክለው እርምጃቸው እንዲገታ እያደረገ የሚገኝ መሆኑንም ገልፀዋል። በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች ሰዎች በሌሉባቸው ቦታዎች እና ጊዜያት የሚፈጸሙ መኾናቸው የፍርድ ሂደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች ገልፀዋል።

በሕፃናትና በሴቶች  መብት ዙሪያ  እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል መሻሻል አለባቸው የተባሉ የሕግ እና አፈፃፀም ጉዳዮች መኖራቸው ተነስተው በስፋት  ውይይት ተደርጎባቸዋል። በመጨረሻም በሀገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን የሴቶች እና ሕፃናት ጥቃቶች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል” ያሉት ሚንስትሯ ችግሩን ለመቀነስ ማኀበረሰቡ በተለይም የፍትሕ አካላት ከፍተኛ ኀላፊነት እንዳለባቸው ገልፀው በቀጣይ ከፍርድ ቤቶችና ከሌሎች የፍትህ አካላት ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ገልፀዋል ።

 

Please follow and like us: