ወጣቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግና ህይወታቸውን መለወጥ የሚችሉበት ዕድል በእጃቸው ላይ ስላለ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል – ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

ከፍታ የወጣቶች የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ተገኝተው መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት በቅንጅት እያከናወነ ይገኛል። ከአምረፍ ሄልዝ አፍሪካ -ኢትዮጵያ ከፍታ የተቀናጀ የወጣቶች ልማት ፕሮጀክት ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ፥ ወጣቶችን በአኮኖሚ ለማብቃት እና የአካል ጉዳተኞችን አካታችና ተጠቃሚ ለማሳደግ፣ በጤናና በሌሎችም መስኮች ፕሮጀክቱን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ባለፉት ጊዜያት በተሰሩት ስራዎች መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበርም የወጣቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል። ወጣቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግና ህይወታቸውን መለወጥ የሚችሉበት ዕድል በእጃቸው ላይ መኖሩን ጠቁመው ይህን ዕድል በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል። አሁን ላይ በተለይ የወጣቶች የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነት እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቁመው በችግር ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ተደራሽ ለማድረግ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህ ረገድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከግንቦት እስከ ግንቦት የሚካሄድ የንቅናቄ መርሃ ግብር ማስጀመሩን አንስተው በፕሮጀክቱ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ወጣቶች ከስራዎቻቸው ጎን ለጎን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የዜግነት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። ለወጣቱ ተጠቃሚ የሚደረጉትን ጥረቶች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይደግፋል ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ፥ ወጣቶቸን በማብቃት ረገድ ከዩኤስ ኤድ፣ አምረፍ ሄልዝ አፍሪካ – ኢትዮጵያ እና ሌሎችም አጋር አካላት በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። በዕለቱ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወኑ የልማት ተግባራትና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ የልምድ ልውውጥ፣ የፖናል ውይይትና የስራ ጉብኝት ተካሂዷል። በመርሃ ግብሩ ላይ ፕሮጀክቱ እየተተገበረ ከሚገኝባቸው 18 ከተሞች የተውጣጡ ተጠቃሚ ወጣቶች፣ የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

Please follow and like us: