የአረጋውያንን ባህሪያት ማወቅ እና መደገፍ የቤተሰብ ታላቅ ሚና ነው!!

የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከልጅነት እስከ እውቀት በተለያዩ ማህበራዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳዮች የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚያልፍ ነው፡፡ በልጅነት ዘመን የሚስተዋሉ ባህሪያት እድሜ ይለውጣቸዋል፡፡ እንደ ሁኔታው ባህሪያቱ ይበልጥ ይጠናከራሉ ወይም ሙሉ በሙሉ ይቀየራሉ፡፡

አንድ ሰው እድሜው ወደ አረጋዊነት ዘመን በደረሰ ቁጥር የባህሪ ለውጦች ሊታይበት ይችላል፡፡ እነዚህም ለውጦች በቤት ውስጥ አረጋውያንን ስንንከባከብ ልናውቃቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ የእነኚህ ባህሪያት መነሻ ምክንያታቸው ከሚሰሙ እና ከሚታዩ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች፣ ከጤና እና ከኢኮኖሚ አቅም ጋር ሊገናኙ ይችላሉ፡፡ ቀድሞ የነበሩ በቀላሉ የማየት፣ የመስማት፣ የማስታወስ እና መሰል የጤና እክሎች ከሰዎች ጋር የመግባባት ሂደታቸውን ሊያከብደው ስለሚችል በብዙ አረጋውያን ላይ የባህሪ ለውጦች ይንጸባረቃሉ፡፡ በቤትዎ አረጋውያን ወይም እድሜየቸው 60 እና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች አሉ? ከሆነ የሚከተሉትን ባህሪያት ሊመለከቱ ስለሚችሉ በዛው ልክ እንክብካቤዎን ያስተካክሉ፡፡ እነዚህም፦

፩/ ስሜታዊ መሆን፡ ስህተቶች ሲታዩ አብዝቶ መተቸት፣ መንቀፍ፣ በሌሎች ጉዳይ አላስፈላጊ አስተያየት መስጠት እና ያንንም በሰዎች ፊት በተደጋጋሚ የማንጸባረቅ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡

፪/ብስጭት እና ቁጣ መሆን፡ ምናልባት በእለት ተእለት ግንኙነት ወቅት ሌላው የቤተሰብ አባል ሳያውቅ ነገር ግን አረጋውያኑ በሚቸገሩበት ምክንያት ብስጩ እና ቁጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ለአረጋውያኑም ሆነ ለቤተሰቡ አባል መልካም አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህ የማይቀር ባህሪ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

፫/ ለመተባበር አለመፍቀድ፡ በተለያዩ ምክንያቶች ለተለያዩ ጉዳዮች እምቢ የማለት ባህሪያቶች ይንጸባረቃሉ፡፡ በእነኚህ ሁኔታዎች ምናልባት በቤት ውስጥ ችግር አለመኖሩን በቅድሚያ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡

እኒኚህ ነገሮች ሲከሰቱ ለጊዜውም ቢሆን በቅርበት መራቅ፣ በእርጋታ እና በትዕግስት መያዝ፣ የሚወዱትን ነገር ማድረግ፣ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እና እንዲደመጡ ማድረግ፣ መንፈስን የሚያረጋጉ እና ውስጣዊ ሰላምን የሚሰጡ የሚወዷቸውን ነገሮችን መከወን፣ የሚጠሉትን ነገር በፊታቸው አለማድረግ እንዲሁም ከአቻዎቻቸውና ከሌሎች ሰዎች ጋር ጊዜ እንዲኖራቸው ማድረግ በመፍትሔነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም አረጋውያን በእነኚህ ባህሪያት ምክንያት ድብርት፣ ብቸኝነት እና ሌላ የጤና እክል ሊገጥማቸው ስለሚችል በወቅቱ የጤና ክትትል ማድረግና ህክምና እንዲወስዱ ማስቻል ይገባል። አንዳንድ ጊዜ የቤተሰብ አባላት እነኚህን ባህሪያት ጠንቅቀው ባለማወቃቸው የተነሳ ስሜታዊ የሚሆኑበት አጋጣሚ ሲፈጠር ይስተዋላል፡፡ ለመሆኑ እናንተ በአረጋውያን ላይ ምን አይነት ባህሪያትን ትመለከታላችሁ፤ እንዴትስ ነው መፍትሔ እየሰጣችሁ የምትገኙት?

ፅሁፉ መጠነኛ ግንዛቤ እንደጨበጣችሁና እነኚህ ችግሮች በሂደት እንደሚስተካከሉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

 

Please follow and like us: