የሚዲያ ተቋማት በአረጋዊያን የማህበራዊ ጥበቃ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለፁ

መስከረም 21 በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአረጋዊያን ቀን ምክንያት በማድረግ አረጋዊያን ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሠሩ የሚዲያ ተቋማት ጋር ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱም መገናኛ ብዙኃን የአረጋውያንን ጉዳዮች ያካተተ ሚዛናዊ የስርጭት ሽፋን እንዲኖራቸው በሚቻልበት ሁኔታ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል። በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቤተሰብና የአረጋውያን ጉዳይ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ በዚሁ ጊዜም፥ አረጋውያን የሀገር ባለውለታ በመሆናቸው ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው፥ ማህበራዊ ደህንነታቸው ተጠብቆና ክብርን ተላብሰው፣ የመሥራት አቅም ላላቸው ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረላቸው ቀሪ ዕድሜያቸውን በደስታ እንዲያሳልፉ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ለአረጋውያን የሚሰጡ የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶች የሰብዓዊ መብት ጉዳይ እንጂ ችሮታ አይደለም ያሉት ኃላፊው በተለይ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ለሆኑ አረጋውያን ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአረጋውያን መብቶች እንዲታወቁና እንዲከበሩ የአድቮኬሲና የንቅናቄ ስራዎችን ከመስራት በተጨማሪ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበርና ሀብት በማሰባሰብ ለማህበራዊና አኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡትን ለመደገፍ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል። በቀጣይም ይህንኑ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተለይም ለአረጋውያን ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ፣ በሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት ረገድ ያላቸውን ሚና በማሳደግ፣ በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲሁም በአረጋውያን ዙሪያ የሚሰሩ አደረጃጀቶችንና ተቋማትን በመደገፍና በማጠናከር መታቀዱን ጠቁመዋል። በመሆኑም ህብረተሰቡን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ለስኬታማነቱ እንዲተባበሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ የሚዲያ አካላት ከተደራሸነታቸው አኳያ ሚዛናዊ ሽፋን በመስጠትና ቋሚ የአየር ጊዜ በመመደብ የአረጋውያን ጉዳይ ተገቢው ትኩረት እንዲያገኝ በማስቻል ብሎም የህብረተሰቡን አመለካከት በመቅረፅና ለበጎ ስራ በማነሳሳት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። በመድረኩ በአረጋውያን መብት እንዲሁም የሚዲያ ተቋማትና ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በአረጋውያን ዙሪያ እየተሰሩ ባሉና በቀጣይ ተግባራት ዙሪያ ምክክርና የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል። የሚዲያ ተቋማት በአረጋዊያን የማህበራዊ ጥበቃ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በውይይቱ ወቅት ገልፀዋል።

Please follow and like us: