የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወሲባዊ ጥቃት አድራሾች ብሔራዊ መረጃ ስርዓትን ወደ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ ።

ብሔራዊ ወሲባዊ ጥቃት አድራሾች መረጃ ስርዓትን
ወደ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችል ስምምነት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣በፍትሕ ሚኒስቴር፣ እና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መካከል ተደርጓል ።

በዕለቱ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚኒስቴር ድኤታ ማዕረግ የሚኒስትሯ አማካሪ አቶ ጌታቸው በዳኔ እንደገለፁት ስርዓቱ ባጠቃላይ በማሕበረሰቡ ውስጥ የወሲብ ጥቃትን ለመቀነስና በተለይ በግለሰብ የሚደረግ ዳግም የወሲብ ጥቃትን ለመቆጣጠር ታስቦ የተሰራ ሲሆን የወንጀል አድራሾች ምዝገባ መረጃ አጠቃቀም የሚያሻሽልና የወሲብ ጥቃት ታራሚዎች የእስር ቆይታ ካበቃ በኋላ ድጋፍ እንዲያገኙ ያመቻቻል ብለዋል።
በስምምነቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
ሲስተሙን ለማልማት የሚያስፈልጉ መረጃዎችን በወቅቱ ከመስጠት ጀምሮ ፣ከመረጃ ስርኣቱ ጋር የተያያዙ የፖሊሲ ጉዳዮችን፣አዋጆችን እና መመሪያዎች እንዲሻሻሉ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም ከሲስተሙ የሚገኘውን ሪፖርት እንደ አስፈላጊነቱ ሚኒስቴር መ/ቤቱ እየተነተነ መረጃውን ለፖሊሲ ማሻሻያ፣ ለማህበረሰብ ግንዛቤ፣ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም የመከላከል ስራዎች ላይ የመጠቀም መብት ይኖረዋል፣ ከመረጃ ስርዓቱ የሚገኘውን ግብዓት መሰረት በማድረግ በተደጋጋሚ ለወሲባዊ ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችና የማህበረሰብ ክፍሎችን በመለየት የግንዛቤ ማስጨበጫና የመከላከል ስራዎች እንደሚያከናውን በስምምነቱ ከተካተቱት ነጥቦች መካከል ይገኛል።

በፍትህ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት በርካታ መረጃዎችን የሚያመነጭ፣ የሚይዝ እና የሚያስተዳድር እንደሆነ ገልጸው በአሁኑ ወቅት የወንጀሎች የምርመራና የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ማበልጽግ ሂደት መጀመሩን ገልፀዋል::

የድሬዳዋ ዮኒቨርስቲ አካዳሚክ ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት መገርሳ ቃሲም( ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ በወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ሶፍትዌሮች እያበለጸገ የሚገኝ ሲሆን በአሁን ወቅትም በሴቶችን ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የምርመራና የመረጃ ስርዓት እንዲሁም የወጣት ጥፋተኞች ሀገራዊ መረጃ ስርዓት የማበልጸግ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

Please follow and like us: