አራተኛው የብሪክስ አገራት የሴቶች ፎረም በሩሲያ ተካሄደ

በአራተኛው Eurasian womens Forum የ BRICS አባል ሀገራት እና ከ126 ሀገሮች የተውጣጡ ተወካዮች በተገኙበት ስብሰባ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ተሳትፎ አድርጓል።

በፎረሙ ‘የማህበራዊ ልማትና ሴቶች’ በሚል ርዕስ በተደረገ ውይይት የኢትዮጵያን ተሞክሮ ማቅረብ ተችሏል። በዋናው የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ወክለው በተገኙ አመራሮችም ‘ሴቶችና አመራር’ በሚል ርእስ በአገራችን የተሰሩ ስራዎች፣ የተገኙ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ተግባራትም ተብራርተዋል። ኢትዮጵያ እንደ ብሪክስ አባል አገርነቷ የትብብርና ቅንጅት ስራዎችን በተመለከተም ተሞክሮዎችን ከመለዋወጥ ባሻገር በጋራ ሊተገበሩ የሚችሉ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችም ታሳቢ መደረግ እንዳለባቸው መልዕክት ማስተላለፍ ተችላል።

አባል ሀገራት የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን በማምጣት ረገድ የተሞክሮ ልውውጥ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በየሀገራቱ የሚተገበሩ ስትራቴጂዎች፣ የወጡ የህግ ማዕቀፎችና ፕሮግራሞች ቀርበው ውይይት የተካሄደ ሲሆን በፎረሙ ላይ እንደ አገር የነቃ ተሳትፎ ተደርጓል። መድረኩ የሀገራችንን ተሞክሮ ማካፈልና ከሌሎችም ጠቃሚ ልምዶችን መውሰድ የተቻለበት እንደነበር ተመላክቷል። በፎረሙ ላይም ከ126 አገራት የተውጣጡ ከ1500 በላይ ልዑካን የተሳተፉ ሲሆን በማጠቃለያው መድረክም በቀጣይ በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል የትብብርና የአጋርነት ስራዎች ተጠናክረው በሚቀጥሉበት እንዲሁም የስርዓተ-ፆታ ልዩነትን በማጥበብና ሴቶችን በማብቃት ረገድ የጋራ ስራዎችን ለማጠናከር የጋራ አቋም በመያዝ ስብሰባው ተጠናቋል፡፡

 

Please follow and like us: