የሀገር ባለውለታ ለሆኑት አረጋውያን ተገቢውን ክብርና ፍቅር መስጠትና ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ

የሀገር ባለውለታ ለሆኑት አረጋውያን ተገቢውን ክብርና ፍቅር መስጠት፣ መብታቸውንና ጥቅማቸውን ማስከበር ብሎም ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክብርት ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።

በበዓሉ ላይ የተገኙት ክብርት ፕሬዝደንት ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ፤ አረጋዊያን ባሳለፉት ረጅም የእድሜ ዘመናቸው ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ለልማት ያዋሉ የህዝብና የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን ገልፀዋል። አቅማቸው በደከመ ጊዜ በተለይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የሀገር ባለውለታ አረጋውያንን መደገፍና መንከባከብ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል። እውቀታቸውንና ልምዳቸውን ማስተላለፍ የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት የትውልድ ቅብብሎሹ እንዲቀጥል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ በበኩላቸው፤ አረጋውያን ከእድሜ ጋር ተያይዘው ልዩ ልዩ ፈተናዎች የሚገጥሟቸው ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍና ፍላጎቶቻቸውን በሚፈለገው መልኩ ለማሟላት መንግስት አበረታች እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአረጋውያንን ጉዳይ የሚከታተልና የሚያስተባብር ክፍል በመሪ ስራ አስፈጻሚ ደረጃ በማደራጀት መዋቅሩን እስከታች ለመዘርጋት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የአሰራር ማዕቀፎችን የመቅረጽና የአስፈጻሚ አካላትን አቅም የማጎልበት ስራ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በቀጣይም ለአረጋውያን የተሻለ ተጠቃሚነት በተለያዩ አካላት ለሚያደረጉ ጥረቶች ስኬታማነት አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር ምክትል የቦርድ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ጌታቸው ክፍሌ፤ አረጋውያን በመጦሪያ ዘመናቸው የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታትና ለመደገፍ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአረጋውያን እና አቅመ ደካሞችን ቤት ለማደስና አዲስ ለመገንባት፣ በማዕከል ደረጃ ድጋፍና ክብካቤ እንዲያኙ ለማድረግ እና ተሳትፏቸውን ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ጠይቀዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ በአረጋውያን ዙሪያ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ግለሰቦች፣ አደረጃጀቶች እና ተቋማት እውቅናና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን በክልሉ ለተቋቋመው የአረጋውያንና ጡረተኞች ማህበር ማጠናከሪያ የሚውል የ1መቶ 50 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አበርክቷል።

Please follow and like us: