መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት መዘዙና መፍትሔው

ሰዎች ለስራና ለተሻለ ህይወት ፍለጋ ሲሉ በሀገር ውስጥ አንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ወይም ድንበር በማቋረት ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተፈጥሯዊና ህገ-መንግስታዊ መብት እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም ይህ የሰው ልጆችን የሚያደርጉ እንቅስቃሴ በሁለት መንገድ የሚፈጸም ሲሆን መደበኛ የሆነ እና መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ተብለው ይታወቃሉ፡፡ መደበኛ ፍልሰት ማንኛውም ፍልሰተኛ የሚሄድበትን ሀገር ህግ አክብሮ አስፈላጊ መረጃዎችን በማሟላት ለትምህርት፣ ለስራ ፣ ለህክምና ፣ ለትዳር ወዘተ የሚደረግ የፍልሰት አይነት ነው፡፡

ይህ የፍልሰት ዓይነት የፍልሰተኞችን መብት ለማስከበር፣ ፍልሰተኞችም ራሳቸው፣ ቤተሰባቸውና ሀገራቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉበት የፍልሰት ዓይነት ነው፡፡ አንጻሩ በደላሎች፣ በህገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች (Traffickers) ወይም በህገ-ወጥ መንገድ ሰው ድንበር የሚያሻግሩ ሰዎች (Smugglers) የሚሰጧቸውን የተሳሳተ መረጃ በመቀበል መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ከሃገር ለመውጣት የሚጥሩ ወጣቶች፣ ሴቶችና ታዳጊ ህፃናት ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ እነዚህ ዜጎቻችን በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ በድንበር ጠባቂዎችና ሌሎች የተደራጁ አካላት እጅ እየወደቁ ከፍተኛ ለሆነ የስነ-ልቦናና የአእምሮ ጤና ችግር፣ ለዝሙት አዳሪነት፣ ለግዳጅ ጋብቻ፣ ከአካል ክፍሎቻቸው መስረቅ፣ ለግዳጅ ሥራ ፣ ለባርነት ወይም ከባርነት ጋር የሚመሳሰሉ ብዝበዛዎች፣ ዘላቂነት ላለው የአካል ጉዳትና ለሞት የሚዳርጉ ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ሲጋለጡ ይስተዋላል። ለችግሩ የበለጠ ተጋላጭ የሚሆኑት በሴቶችና በህጻናት እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ደህንነቱ በልተጠበቀና አስተማማኝ ባልሆነ ጉዞ መስመርን በመከተል በህገ-ወጥ መንገድ በሚደረግ ጉዞ በጀልባ መገልበጥ፣ በርሃዎችን በሚያቋርጡበት ጊዜ በርሃብና ውሃ ጥም፣ ከዚህም አለፈው በተላለፊያና በደራሻ ሀገራት ሲደርሱ በድንበር ጠባቂዎች በተኮስ ጥይት ህይወታቸውን ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ በቅርቡ በጂቡቲ ባህር ዳርቻ ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ በነበሩ ዜጎች ላይ የተከሰተው አደጋ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

መንግስት እያካሄደ ባለው ዜጋ ተኮር ፖሊሲ ከ2016 ጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከሱዳን፣ ከየመን፣ ከኦማን እና ከሊባኖስ 145,380 በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር መመለሱ ሌላኛው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ያስከተለው አሉታዊ ውጤት መሆኑን ልብ ይሏል። ድርጊቱ በዜጎች ላይ ከሚደርሰው አካላዊና ሰብአዊ ጉዳት ባለፈ በሀገሪቱ ገፅታ ላይም የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በጉዳዩ አሳሳቢነት ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ሰፊ ጥረት እየተደረገና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ቢሆንም ዛሬም መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት/በህገወጥ መንገድ የሚደረግ ፍልሰትና ስደት እንደቀጠለ ይገኛል። ታዲያ ዜጎች በኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ በግንዛቤ ማነስ፣ በአቻ እና በቤተሰብ ግፊት ምክንያት አሊያም በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ተታለው ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ እየሆኑ የሚቀጥሉት እስከመቼ ድረስ ነው? እንደሚታወቀው በሀገራችን በሰው መነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ድርጊት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012 መሠረት ተግባሩ የወንጀል ድርጊት መሆኑ በግልፅ ተደንግጓል።

ዓላማውም ብዝበዛና ትርፍ ማግኘት ላይ ያተኮረ እንጂ የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ ታስቦ በቀናዒነት የሚከወን ድርጊት እንዳልሆነ መላው ህብረተሰብ በተለይም ደግሞ የሀገራችን ሴቶችና ወጣቶች በውል መገንዘብና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።  የሀገራችን ሴቶችና ወጣቶች – በሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል። ለዚህም የአመለካከት ለውጥ ማምጣት፣ በአገር ውስጥ ያሉትን ዕድሎችና መልካም አጋጣሚዎች አሟጦ መጠቀም፣ ትዕግስትን መላበስ፣ ተስፋ አለመቁረጥ፣ ስራን አለመናቅና ተግቶ መስራት ያስፈልጋል። በአንፃሩ ውጭ ሀገር ሄዶ መስራት የግድ እንደአማራጭ የሚወሰድ ከሆነ መደበኛና ህጋዊውን መንገድ መከተል፤ ለዚህ ደግሞ ትክክለኛውን መረጃ ከሚመለከተው አካል ብቻ መውሰድ እንደሚገባ አጥብቀን እንመክራለን። እንደ አጠቃላይ ግን መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከልና በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት በየጊዜው እያደረሰ ያለውን ጉዳትና ሞት ለመቀነስ ራሳቸው ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻና አጋር አካላት በቅንጅት እንዲረባረቡ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪውን ያቀርባል፡፡ በቀጣይም መንግስት በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ጠንካራ እርምጃ መወሰድ እንዲችል ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መልዕክቱን ያስተላልፋል።

Please follow and like us: