የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ አቅርቦትን ለማሳደግ፣ አቅምን ባገናዘበ እና ንፅህናውን በጠበቀ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ ያሉ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታታትና መደገፍ ይገባል – ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና በኢትዮጵያ የቱርክዬ አምባሳደር እና የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካይ ክቡር በርከ ባረን የቲም የህፃናት እንክብካቤ ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባውን የሴቶች የንህፅና መጠበቅያ መስሪያ ማዕከል መርቀው ከፍተዋል፡፡
በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የወር አበባ ለሴቶች የተፈጥሮ ጸጋና ትውልድን ለማስቀጠል ከፈጣሪ የታደሉት የህይወት ክፍል ቢሆንም በንፅህና መጠበቂያ ምርት ላይ በሚስተዋለው የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ምክንያት ሴቶችና ልጃገረዶች ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሳደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከመንግስት ጥረት ጎን ለጎን ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም የግል ባለሃብቶችና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑንም አድንቀዋል፡፡
የቲም የህፃናት እንክብካቤ ማዕከል በዛሬው እለት በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ለማምረት የሚያስችል ማዕከል አስመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉ ለዚህ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በቀጣይም የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ አቅርቦትን ለማሳደግ፣ አቅምን ባገናዘበ እና ንፅህናውን በጠበቀ መልኩ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ክብርት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናግረዋል።  ችግሩን በዘላቂ ለመፍታትም በቀጣይ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታታትና መደገፍ፣ አዳዲስ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲገቡ ማስቻል፣ የአጋር ድርጅቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ በስርጭት ሂደት ያሉ ችግሮችን መፍታት እንዲሁም በወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ላይ ያተኮረ ጥናትና ምርምር እንዲካሄድ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በወር አበባ ላይ ያለውን መገለል ለመስበር እና ጤናማ ልምዶችን ለማሳደግም ለማህበረሰቡ ትምህርት ከመስጠት ጎን ለጎን በትምህርት ቤቶችና በስራ ቦታዎች አካባቢ ለወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ምቹ እንዲሆኑ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የቲም የህፃናት እንክብካቤ ማዕከል መስራችየ ሆኑት አቶ ከማል አብዱልሀኪም በበኩላቸው ማዕከሉ ለማህበረሰቡ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡በኢትዮጵያ የቱርክዬ አምባሳደር እና የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካይ ክቡር በርከ ባረን፥ በቀጣይም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች 5ሺህ የንጽህና መጠበቂያ ፓድ ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም ይኸው ስራ በሌሎች ክልሎች ለማስጀመር እቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡
Please follow and like us: