በህጻናት ማሳደጊያ ተቋማትና ከወላጆቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት የሚገኙ ህጻናት አያያዝን አስመልክቶ የክትትልና ድጋፍ ስራ መሰራቱ ተገለጸ

በህጻናት ማሳደጊያ ተቋማትና ከወላጆቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት የሚገኙ ህጻናት አያያዝን አስመልክቶ የክትትልና ድጋፍ ስራ መሰራቱ ተገለጸ
(አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2015 ዓ.ም) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር በህጻናት ማሳደጊያ ተቋማትና በማረሚያ ቤት የሚገኙ ህጻናት አያያዝን አስመልክቶ የክትትልና ድጋፍ ስራ መሰራቱ ተገለጸ።
የክትትሉ ዋና ዓላማ በየተቋማቱ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታን ለማሻሻልና ህጻናት በተለያዩ አማራጭ የድጋፍና ክብካቤ ፕሮግራሞች ያላቸውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሆነ በህጻናት መብትና ጥበቃ መሪ ስራ አስፈጻሚ የህጻናት ድጋፍ አገልግሎት ማስፋፊያና ማጠናከሪያ ዴስክ ኃላፊው አቶ ሀሰን መሀመድ ተናግረዋል።
የክትትል ስራው ከታህሳስ 25 እስከ ጥር 08/2015 ዓ.ም በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሀዋሳ ከተማ በሚገኙ 6 የህጻናት ማሳደጊያዎችና ማረሚያ ቤት እንዲሁም በደ/ብ/ብ/ህ/ ክልላዊ መንግስት በወላይታ ዞን በሚገኙ 6 የህጻናት ማሳደጊያዎችንና ማረሚያ ቤት ላይ መካሄዱን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰበታ ልዩ ዞን ባሉ 3 የህጻናት ማሳደጊያዎችና ማረሚያ ቤት፣ በሱሉልታ 1 የህጻናት ማሳደጊያ፣ በቡራዩ 2 የህጻናት ማሳደጊያዎች፣ በሎሜ 1 የህጻናት ማሳደጊያ እና በአዳማ ከተማ በሚገኙ 4 የህጻናት ማሳደጊያዎችና ማረሚያ ቤት ላይ የድጋፋዊ ክትትል ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
እንደኃላፊው፤ በአጠቃላይ በ24 የህጻናት ማሳደጊያዎችና በ4 ማረሚያ ቤቶች ላይ የህጻናት አያያዝና የእንክብካቤ አገልግሎት አስጣጥን በተመለከተ ክትትልና ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ተቋማቱ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች እንዲያስቀጥሉና ክፍተቶችን እንዲስተካክሉ ተገቢው ግብረ-መልስ መስጠት ተችሏል፡፡
የህጻናት ማሳደጊያ ተቋማትም ሆኑ ማረሚያ ቤቶች ለህጻናት የሚሰጡት አገልግሎት በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት መሆኑን ለማረጋገጥና ለማሻሻል እንዲያስችል የክትትልና ድጋፍ ስራው በሌሎችም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው አቶ ሀሰን መሀመድ አስታውቀዋል።
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *