ሚኒስትሯ ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ብሔራዊ ጀግኖች የጤና ባለሙያዎች ፓርክና መታሰቢያ ሐውልት መረቀው ከፈቱ

(አዲስ አበባ፣ ጥር 18/ 2015 ዓም ) የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በጦርኋይሎች ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ለብሔራዊ ጀግኖች የጤና ባለሙያዎች የተገነባውን ፓርክና መታሰቢያ ሐውልት በዛሬው ዕለት መረቀው ከፈቱ።
ረፋዱ ላይ በተካሄደው የምረቃ ስነስርዓት ላይ ሚኒስትሯ ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት “የኢትዮጵያ ጀግኖች የውስጥና የውጭ ጠላት አብረው በተነሱበት ወቅት ሁሉ አንጀታቸውን ለረሀብ፣ እግራቸውን ለእሾህና ለጠጠር፣ ግንባራቸውን ለጥይት አጋልጠው እናት ሀገራቸውን አሳልፈን አንሰጥም ነፃነታችንንም ለጊዜያዊ ጥቅም አንለውጥም ብለው ለህይወታቸው ሳይሳሱ ፊት ለፊት የተጋፈጡ በዱር በገደሉ እየተዋደቁ በከፈሉት መስዋዕትነትና ባካሄዱት መራር ትግል ድልን እንድንጎናፀፍ ያደረጉንና በክብር አገራችንን ያቆዩልን በመሆኑ ክብር ይገባቸዋል” ሲሉ ገልፀዋል።
የዛሬ ትውልድም ፈለጋቸውን ተከትሎ ሰላም በደፈረሰበት ሁሉ ፈጥኖ እየደረሰ ከሀገር አልፎ በታላላቅ አህጉራዊና አለም አቀፍ ግዳጆች ላይ ጭምር በመሰማራት አኩሪ ገድል እየፈፀሙ ይገኛሉ ብለዋል።
የመታሰቢያ ሐውልቱም መልካም የሰሩ ሀገር ወዳድ ጀግኖቻችንን እና ሙያዊ ኋላፊነታቸውን የተወጡንና በቀጣይም እየተወጡ የሚገኙትን የምናስታውስበትና የምንዘክርበት ተምሳሌታዊ ማሳያ እንደሆነም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ሁሉም ዜጋ የሀገር ባለውለታ ለሆኑ ጀግኖች እና ለጀግኖች ቤተሰቦች ለከፈሉት መስዋዕትነት የሚመጥን ክብር፣ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያደርግ ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘላቂነት ባለው፣ ስርዓት በተዘረጋለት አግባብ እና ከፍ ባለ ማህበራዊ ትጋት እንደሚሰራ ገልፀው
ለዚህም ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ፣ ማህበራዊ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅና ህይወታቸውን ለማሻሻል የሚያስችል አዋጅ ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን መዘጋጀቱንና ለሚኒስትሮች ም/ቤት መቅረቡን አስታውቀዋል።
አዋጁ ፀድቆ በስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ያሉት ሚኒስትሯ መንግስትም ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ መሆኑን አያይዘው ገልፀዋል።
ብሔራዊ የጀግኖችና ህፃናት አምባ ድርጅት እና ሌሎች የበጎ አድራጎት ተቋማት ሰራዊቱን በመደገፍም ሆነ ይህን መታሰቢያ በማኖር ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ ከልብ አመስግነዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የመከላከያ ሚኒስቴር የስራ ኋላፊዎች፣ ብሔራዊ የጀግኖችና ህፃናት አምባ ድርጅት የቦርድ አባላት፣ የበጎ አድራጎት ተቋማት ተወካዮች ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የጤና ባለሙያዎችና በህክምና ላይ የሚገኙ የጦር ጉዳተኞች ተገኝተዋል።
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *