በቦረና ዞን በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ115 ሚሊዮን ብር በላይ ሰብዓዊ ድጋፍ ተደረገ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዘንድሮ ለ47ኛ ጊዜ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል የተከበረውን አለም አቀፍ የሴቶቸ ቀንን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቦረና ዞን በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ115 ሚሊዮን ብር በላይ ሰብዓዊ ድጋፍ መደረጉን ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ አስታወቁ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዓሉን በማስመልከት ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ገቢዎች ኮሚሽን እና ከጤና ሚኒስቴር በጋራ በመሆን የችግሩን ስፋት ለመገንዘብና ሰብዓዊ ድጋፍን ለማጠናከር እንዲቻል በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን በትላንትናው ዕለት የመስክ ጉብኝት መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡
ጉብኝቱን ተከትሎም በኩዌት ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የተገኘውን 450,000 ብር ጨምሮ ከፊዴራል ተቋማቱ ጋር በጋራ በመሆን በጥቅሉ ከ115 ሚሊዮን ብር በላይ በድርቅ ምክንያት ለከፋ ችግር ለተጋለጡ ዜጎች ድጋፍ መደረጉንም ሚኒስትሯ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ተቋማትን፣ ህብረተሰቡንና የልማት አጋራትን በማስተባበር በድርቁ ሳቢያ የተጎዱና የተፈናቁሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ህይወታቸውን ለመታደግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራልም ብለዋል፡፡
ማህበረሰባችን ከገጠመው አስከፊ ፈተና ለማሻገር ሁሉም እንዲተባበርና የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣም ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *