ጆይፉል ላይፍ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕጻናት የልህቀት ማዕከል ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ተጣለ

(የካቲት 20/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ) በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጆይፉል ላይፍ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህጻናት ሕጻናት የልህቀት ማዕከል ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ተጣለ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትርን በመወከል የሚኒስቴር ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ እታገኘሁ አሰፋ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደሚታወቀው የአብራካችን ክፋይና የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑት ህፃናት አካላዊ፣ አእምሯዊና ስነልቦናዊ ደህንነታቸው ተጠብቆ ሁለንተናዊ ሰብዕናቸው በመልካም  ስነ-ምግባርና በእውቀት ታንጾ ጤናማ፣ ምርታማና ሀገር ወዳድ ዜጎች እንዲሆኑ ሁላችንም እንመኛለን፡፡

አክለውም ይሁንና  በተፈጥሮም ሆነ ከጊዜ ወለድ በሆኑ ምክንያቶች ሳቢያ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ህጻናትን ጤናማና ሁለንተናዊ እድገት እየተፈታተኑ ካሉ አያሌ  ችግሮች መካከል ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት ጉዳይ አንዱ ሲሆን ይህም ህጻናቱንና ቤተሰቦቻቸውን ተደራራቢና ውስብስብ ለሆኑ ችግር ሲዳርጋቸው ይስተዋላል በማለት፡፡ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት የገጠማቸው አካላዊ አሊያም አእምሯዊ እክሎች በራሳቸው የሚያስከትሏቸው ዘርፈ-ብዙ እንቅፋቶች ከመኖሩም ባሻገር በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ አመለካከትና መገለል ለከፍ የስነልቦና ጫና የሚዳርጋቸው በመሆኑ ችግሩን በተቀናጀ አግባብ መፍትሄ ማበጀት፤ ከንፈር ከመምጠጥ በዘለለም በህጻናቱ ህይወት ላይ ትርጉም ያለውና በተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ይገባናል በማለት አስገንዝበዋል፡፡

የጆይፉል ላይፍ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሪት ሰብለወንጌል በቀለም ህይ ድርጅት ለአስራ ስምንት አመት በኪራይ ቤት ሲያገለግል መቆቱን አንስተው ልዩ ፍላጎት ያለባቸው ህጻናት ለማገልገል ምቹ ያለመሆኑን ገልጸው በአሁን ሰዓት ደግሞ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ በ500 ካ.ሜ ላይ ጆይፉል ላይፍ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለመገንባት መሰረተ ድንጋይ መጣሉን ገልጸው ሁሉም መንግስትም፣ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በመገንባት ልዩ ፍላጎት ለሚሹ ልጆች እንድረስላቸው በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *