የከተማ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት ውጤታማነትን ለማሳደግና ለማጠናከር ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል

የከተማ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት ውጤታማነትን ለማሳደግና ለማጠናከር ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል

(ቢሾፍቱ፣ መጋቢት 7/2015 ዓም) የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ የሚሰጡ የቋሚና የጊዜያዊ ቀጥታ ድጋፍ አገልግሎት በማሻሻል የፕሮጀክቱን ውጤታማነትን ለማሳደግና ለማጠናከር እንዲያስችል በቢሾፍቱ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

በስልጠና መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ እንደተናገሩት፤ ስልጠናው በዋናነት በዘርፉ የተሰማሩ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ፈጣን፣ ቀልጣፋና ውጤታማ አሰራር በመዘርጋት ለተጠቃሚ ወገኖች የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለማሳለፍና የመፈፀም አቅም ለማሳደግ የበኩሉን እገዛ ያደርጋልም ብለዋል።

ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ እንዲከታተሉና በስራ ላይ እንዲያውሉ ያሳሰቡት ሚኒስትር ዴኤታ ውጤታማ የፕሮጀክት አፈፃፀም እንዲመዘገብ ሚኒስቴር መ/ቤቱ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከድህነት እንዲላቀቁ በማድረግ ራሳቸውን ጠቅመው ለሀገሪቱ ልማት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዲችሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል አመራሮች ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በገንዘብ ድጋፍና መሰረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶች ትስስርን በመፍጠር ረገድ መጠነ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

በቀጣይም ፕሮጀክቱ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ አስተግባሪ አካላት የድርሻውን እንዲወጡ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።

በዕለቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቋሚና የጊዜያዊ ቀጥታ ድጋፍ የገጠርና የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ዴስክ ኋላፊ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው የልዩ ድጋፍ አገልግሎት ማስፈፀሚያ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አማካሪ አቶ ገመቹ ተርፋሳ በአገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርድ ዙሪያ ሰነድ አቅርበው ግንዛቤ እንዲያዝበት ተደርጓል።

ስልጠናው በተለያዩ የልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ሰነዶች ላይ ያተኮረ ሲሆን በስልጠናው መርሀ ግብር ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው ክልሎችና ከተሞች የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *