“ሴቶች በፈጠራና ኢኖቬሽን ዘርፍ ያላቸውን ሚናና ተሳትፎ ለማሳደግ በቅንጅት መስራት ይገባል” – ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

(አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18/2015 ዓ.ም) ሴቶች ኢኖቬሽንና በፈጠራ ዘርፍ ያላቸውን ሚናና ተሳትፎ ለማሳደግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።
የዘንድሮ አለም አቀፉ የአእምሯዊ ንብረት ቀን “ሴቶችና አእምሯዊ ንብረት: ኢኖቬሽንና ፈጠራን ማፋጠን” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች በሳይንስ ሙዚየም እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትሯ ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገራችን በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ሴቶች አዳዲስ ፈጠራዎችን በማመንጨት፣ የስራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ ማህበረሰባዊ ፋይዳ ያላቸውና ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን በማበርከትና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሆኖም ከአእምሮ ንብረት ጋር በተያያዘ ሴቶች የፈጠራ ስራ ነጠቃ እንዲሁም በቴክኖሎጂው አማካኝነት ልዩ ልዩ ፆታዊ ጥቃት ይፈፀምባቸዋል ያሉት ሚኒስትሯ በዘርፉ ያላቸውን ሚና፣ እምቅ አቅምና ተሰጥዖ በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ የሚገጥማቸውን ተግዳሮት ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራሩን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ በአጽዕኖት አሳስበዋል።
በቀጣይ ሴቶች የአእምሮ ፈጠራ ስራዎቻቸው በቂ የህግ እውቅናና ጥበቃ እንዲያገኙ፣ በተደራጀ አግባብ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ፣ ጥረታቸው ለፍሬ እንዲበቃና የድካማቸውም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሀገር የጋራ መግባባት ተደርሶበት የተጀመረው የስርዓተ ፆታ አካቶ ትግበራ ስልት ድርሻው የላቀ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለስኬታማነቱ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
ኢኖቬሽንና ፈጠራ በማፋጠን ረገድ የሴቶችን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ለሚከናወኑ ተግባራት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግም ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልጸዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን
በዓሉ በየአመቱ በአእምራዊ ንብረት፣ ፈጠራና ኢኖቬሽን ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት በሚያስችሉ ተግባራት እየተከበረ እንደሚከበር ተናግረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ዶ/ር ሁሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው መንግስት ፈጠራ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባትና ሴተችን ጨምሮ ለዜጎች የተሻለ ተጠቃሚነት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ አዳዲስ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ በስራ ላይ ማዋሉን ገልፀዋል።
ሚኒስቴር መ/ቤቱም የሪፎርም ስራ በማካሄድ ለተግባራዊነቱም የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግና ሂደቱን በማስተባበር የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዓሉ “እንችላለን” በሚል መርህ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ሴት ፈጣሪዎችን፣ ሃሳብ አመንጪዎችንና ፈር ቀዳጅ የፈጠራ ስራዎችን በመዘከር እየተከበረ እንደሚገኝና ይህም ለሀገራችን ሴት የፈጠራ ባለቤቶች መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አለም አቀፉ የአእምሯዊ ንብረት ቀን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ ወጣት የስራ ፈጠራ ማህበር ጋር በመተባበር በፓናል ውይይት እና የወጣትና ሴት የፈጠራ ስራዎች ማሳያ ኤግዚቢሽን በማካሄድ እየተከበረ ይገኛል።
ዕለቱን አስመልክቶ ሴቶችና አእምሯዊ ንብረት በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ አጭር የውይይት ፅሁፍ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የንግድ ምልክት መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ትዕግስት ቦጋለ ቀርቦ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ከሌሎች ተቋማት በተውጣጡ ፓናሊስቶች ውይይት ተካሂዷል።
Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *